በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች ይዞ ሄደና ማዘንና መጨነቅ ጀመረ። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ እዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው። ወደ ፊት ጥቂት እልፍ ብሎ በፊቱ ተደፋና እንዲህ ሲል ጸለየ “አባቴ! የሚቻል ከሆነ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ አይሁን።” ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፥ ጸልዩም፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ “አባቴ ሆይ! ይህንን ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ፥ ፈቃድህ ይሁን” ብሎ ጸለየ። ዳግመኛ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና። እንደገና ትቶአቸው ሄደ፤ ያንኑ ቃል ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጥቶ እንዲህ አላቸው “ከእንግዲህስ ተኙ፥ ዕረፉም፤ እነሆ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።” ይህንም ገና ሲናገር ሳለ፥ እነሆ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ዱላ ይዘው ከእርሱ ጋር መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! ለምን መጣህ?” አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡና እጃቸውን በኢየሱስ ላይ ጫኑ፥ ያዙትም። እነሆ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህኑን ባርያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና። ወይስ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት አሁን ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነ ‘እንደዚህ መሆን አለበት’ የሚሉት መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ወጣችሁን? ዕለት በዕለት በመቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው የነቢያት መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፥ ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህኑ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ለማየት ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። ሊቃነ ካህናትና ሸንጎው ሁሉ ሊገድሉት ፈልገው በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን አላገኙም፤ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢመጡም ምንም አላገኙም፤ በመጨረሻም ሁለት መጥተው፥ “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል፤” አሉ። ሊቀ ካህኑም ተነሥቶ “እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህኑም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ከሆንህ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥና በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህኑ ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ “ተሳድቦአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን መያዝ ለምን ያስፈልገናል? እነሆ አሁን ስድቡን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ ፊቱ ላይ ተፉበት፥ መቱት፥ በጥፊም መቱት እንዲህም አሉት “ክርስቶስ ሆይ! እስቲ ትንቢት ተናገርልን፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው?” ጴጥሮስም ከቤት ውጪ በግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድ ወደ እርሱ ቀርባ “አንተም ከገሊላዊው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቀውም” ብሎ በሁሉም ፊት ካደ። ሊወጣ ወደ በሩ ሲሄድ ሌላዪቱ አየችውና በዚያ ለነበሩት “ይህም ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ” አለቻቸው። “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ እየማለ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚያ ቆመው የነበሩት ጠጋ ብለው ጴጥሮስን “በእውነት አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤ አነጋገርህ ያስታውቅብሃልና” አሉት። በዚያን ጊዜ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ ይራገምና ይምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ የተናገረውን የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
የማቴዎስ ወንጌል 26 ያንብቡ
ያዳምጡ የማቴዎስ ወንጌል 26
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 26:36-75
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos