የማቴዎስ ወንጌል 23:13-39

የማቴዎስ ወንጌል 23:13-39 መቅካእኤ

“እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! መንግሥተ ሰማያትን በሰዎች ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ፥ አንድ ሰው የእምነታችሁ ተከታይ ለማድረግ በባሕርና በደረቅ ትዞራላችሁ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ታደርጉታላችሁ። “እናንተ ዕውራን መሪዎች ‘ማንም በቤተ መቅደስ ቢምል ምንም አይደለም፥ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል፤’ የምትሉ ወዮላችሁ። እናንተ ዕውሮችና ሞኞች! የትኛው ይበልጣል? ወርቁ ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? ደግሞም ‘ማንም በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ ማንም በላዩ ላይ ባለው መባ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል፤’ ትላላችሁ። እናንተ ዕውሮች! የትኛው ይበልጣል? መባው ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል በመሠዊያውና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ በቤተ መቅደስም የሚምለውም በቤተ መቅደሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ በሰማይ የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በሚቀመጠው ይምላል። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ ምክንያቱም ከአዝሙድ፥ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት ታወጣላችሁ፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ፍርድን፥ ምሕረትንና እምነትን ትተዋላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ እነዚህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውራን መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ ግመልን ግን ትውጣላችሁ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ የጽዋውንና የሳሕኑን ውጭ ታጠራላችሁ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ራስን አለመግዛት ሞልቶባቸዋል። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! ውጭው ንጹሕ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውን ውስጡን አጥራ። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን!ወዮላችሁ፥ በውጫቸው አምረው የሚታዩ በውስጣቸው ግን በሙታን አጥንትና በርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ትመስላላችሁና። እንዲሁም እናንተ በውጭ ለሰው ጻድቃን መስላችሁ ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ሕገ ወጥነት ሞልቶባችኋል። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ፥ የነቢያትን መቃብር ትሠራላችሁ የጻድቃንንም መቃብር ታስጌጣላችሁና፥ ‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር’ ትላላችሁ። እንግዲህ የነቢያት ገዳዮች ልጆች መሆናችሁን ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ፈጽሙ። እናንተ እባቦች! የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ እነሆ እኔ ነቢያትን፥ ጥበበኞችና ጻፎችን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ ትሰቅላላችሁም፥ ከእነርሱም አንዳንዶቹን በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዱአቸዋላችሁ፤ በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው ጻድቅ ደም ሁሉ በእናንተ ላይ ይደርሳል። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል። “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ! ነቢያትን የምትገድዪ ወደ አንቺ የተላኩትንም የምትወግሪ፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ልሰበስብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል። ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች