የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 23:13-39

የማቴዎስ ወንጌል 23:13-39 አማ05

“ሰው ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገባ፥ በሩን የምትዘጉ እናንተ ግብዞች፥ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡበትም፤ መግባት የሚፈልጉትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ!” [ “ለታይታ በምታቀርቡት ረዥም ጸሎት እያመካኛችሁ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች መተዳደሪያ የምትጨርሱ እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ስለዚህ እናንተ የባሰ ፍርድ ይደርስባችኋል።] “እናንተ ግብዞች፥ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! አንድን ሰው የእምነታችሁ ተከታይ ለማድረግ በባሕርና በየብስ ትዞራላችሁ፤ ባስገባችሁትም ጊዜ፥ ከእናንተ በሁለት እጥፍ ይብስ ለገሃነም የተዘጋጀ ታደርጉታላችሁ! “እናንተ ዕውሮች መሪዎች! ወዮላችሁ! ‘ሰው በቤተ መቅደስ ቢምል፥ ምንም አይደለም’ ትላላችሁ፤ ‘በቤተ መቅደሱ ወርቅ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል’ ትላላችሁ፤ እናንተ ሞኞችና ዕውሮች! ከወርቁና ወርቁን ከሚቀድሰው ቤተ መቅደስ የቱ ይበልጣል? እንዲሁም ‘ሰው በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም’፤ ‘በመሠዊያው ላይ ባለው መባ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል’ ትላላችሁ። እናንተ ዕውሮች! ከመባውና መባውን ከሚቀድሰው መሠዊያ የቱ ይበልጣል? ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል፥ በመሠዊያውና በመሠዊያው ላይ ባለው ነገር ሁሉ ይምላል። በቤተ መቅደስም የሚምል፥ በቤተ መቅደሱና በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚኖረው ይምላል። በሰማይ የሚምልም በእግዚአብሔር ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በሚቀመጠው ይምላል። “እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፥ ከእንስላል፥ ከከሙን ዐሥራት ትሰጣላችሁ፤ ነገር ግን በሕግ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ነገሮች ትተዋላችሁ፤ እነርሱም ትክክለኛ ፍርድ፥ ምሕረትና ታማኝነት ናቸው፤ ያንን ሳትተዉ ይህንንም ማድረግ ይገባችሁ ነበር። እናንተ ዕውሮች መሪዎች! ከምትጠጡትም ሁሉ እንደ ትንኝ ትንሽ የሆነችውን ነገር አጥልላችሁ ትጥላላችሁ፤ እንደ ግመል ትልቅ የሆነውን ነገር ግን ትውጣላችሁ! “እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! ብርጭቆውንና ሳሕኑን ከውጪ በኩል ታጠራላችሁ፤ ውስጡ ግን ቅሚያና ሥሥት የሞላበት ነው፤ አንተ ዕውር ፈሪሳዊ! አስቀድመህ ብርጭቆውንና ሳሕኑን ከውስጥ በኩል አጥራ! በዚያን ጊዜ በውጪም በኩል ንጹሕ ይሆናል። “እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! በውስጣቸው በሞቱ ሰዎች አጥንትና በርኩስ ነገር ሁሉ የተሞሉ፥ በውጪ ግን በኖራ ተለስነው የሚያምሩ መቃብሮችን ትመስላላችሁ። እንዲሁም እናንተ፥ በውጪ ለሰው ጻድቃን መስላችሁ ትታያላችሁ፤ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ክፋት ሞልቶባችኋል። “እናንተ ግብዞች፥ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር ትገነባላችሁ፤ የጻድቃንንም ሐውልት ታስጌጣላችሁ። ‘በቀድሞ አባቶቻችን ዘመን ተገኝተን ብንሆን ኖሮ የነቢያትን ደም በማፍሰስ ከእነርሱ ጋር ባልተባበርንም ነበር’ ትላላችሁ። እንግዲህ፥ ነቢያትን ለገደሉ ሰዎች ልጆቻቸው መሆናችሁን ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። እንግዲያውስ አባቶቻችሁ የጀመሩትን እናንተም ፈጽሙ። እናንተ እባቦች፥ እባብ ልጆች፥ እንዴት ከገሃነም ቅጣት ማምለጥ ትችላላችሁ? ስለዚህ እነሆ፥ እኔ ነቢያትን፥ ጥበበኞችን፥ መምህራንን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ፤ አንዳዶቹን ትሰቅላላችሁ፤ አንዳንዶቹንም በምኲራባችሁ ትገርፋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማም ታሳድዱአቸዋላችሁ በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም በምድር ላይ ስለ ፈሰሰው የጻድቃን ደም ቅጣቱ በእናንተ ላይ ይደርሳል፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ ቅጣት በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም ሆይ! አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ! ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ሥር እንደምትሰበስብ፥ እኔም የአንቺን ልጆች በአንድነት ልሰበስብ ስንት ጊዜ ፈቀድኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እንግዲህ እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀራል። ስለዚህ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች