በመንገድ ዳር የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን ከቅጠል በስተቀር ምንም አላገኘባትም፤ “እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይገኝብሽ” አላት። የበለስዋ ዛፍም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህንን አይተው በመደነቅ “የበለስዋ ዛፍ ወዲያውኑ እንዴት ደረቀች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ፥ በበለሲቱ ዛፍ እንደተደረገው ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ትቀበላላችሁ።” ወደ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ ሊቃነ ካህናትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው “እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እኔም ደግሞ አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተ ከነገራችሁኝ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰዎች?” እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተነጋገሩ “‘ከሰማይ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች’ ነው ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያዩት ሕዝቡን እንፈራለን” አሉ። ለኢየሱስም “አናውቅም” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ መጀመሪያውም ሄዶ ‘ልጄ ሆይ! ዛሬ ወደ ወይኔ አትክልት ሥፍራ ሂድና ሥራ’ አለው። እርሱም ‘አልሄድም’ አለ፤ ቆይቶ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ሄዶ እንዲሁ አለው እርሱም ‘እሺ ጌታዬ’ ብሎ መለሰለት፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም “የመጀመሪያው” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ዘማውያን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ ወደ እናንተ መጥቶ ነበር፥ አላመናችሁትም፤ ቀራጮችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ በመጨረሻም ይህንን አይታችሁ እንኳ ልታምኑት ንስሐ አልገባችሁም።
የማቴዎስ ወንጌል 21 ያንብቡ
ያዳምጡ የማቴዎስ ወንጌል 21
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 21:19-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች