የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 21:19-32

የማቴዎስ ወንጌል 21:19-32 አማ05

አንዲት የበለስ ዛፍ በመንገድ ዳር አየና ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ “ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ፍሬ አይገኝብሽ!” አላት። ዛፊቱም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ይህች የበለስ ዛፍ በአንድ አፍታ እንዴት ደረቀች!” በማለት ተገረሙ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁና ባትጠራጠሩ በበለሲቱ ዛፍ ላይ እንደ ተደረገው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህንን ተራራ እንኳ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር!’ ብትሉት ይሆንላችኋል። አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።” ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ያስተምር ነበር። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀረቡና “ይህን ሁሉ የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ይህን ሥልጣን የሰጠህስ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ ለጥያቄዬ መልስ ከሰጣችሁኝ እኔም ይህን ሁሉ በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከየት መጣ? ከእግዚአብሔር ነበረ ወይስ ከሰው?” እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተመካከሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም’ ይለናል፤ ‘ከሰው ነው’ ብንል ደግሞ፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያዩት፥ ሕዝቡን እንፈራለን።” ስለዚህ “አናውቅም” ሲሉ ለኢየሱስ መለሱለት። እርሱም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን ይህን ሁሉ እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ታዲያ ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ከእነርሱ ወደ አንደኛው ቀርቦ፥ ‘ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ወደ ወይን አትክልት ቦታዬ ሄደህ እንድትሠራ ይሁን’ አለው። ልጁም ‘እምቢ አልሄድም’ አለ። ይሁን እንጂ በኋላ ተጸጸተና ሊሠራ ሄደ። አባትየው ወደ ሁለተኛው ልጁ ደግሞ ሄደና እርሱንም እንዲሁ እንዲሠራ አዘዘው፤ ልጁም ‘እሺ አባቴ እሄዳለሁ’ አለ። ነገር ግን አልሄደም። እንግዲህ ከነዚህ ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም “የመጀመሪያው ነዋ!” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ወደ መንግሥተ ሰማይ በመግባት ይቀድሙአችኋል። መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ቢመጣ አላመናችሁትም፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ ይህንንም አይታችሁ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች