የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 10:1-23

የማቴዎስ ወንጌል 10:1-23 መቅካእኤ

ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፥ በሽታንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው። የዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፥ ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፥ ቶማስና ቀራጩ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ፥ ቀናኢው ስምዖንና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸውም፦ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ ይልቅስ ወደ ጠፉት በጎች ወደ እስራኤል ቤት ሂዱ። ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች፤’ ብላችሁ ስበኩ። በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ። ወርቅ ወይም ብር ወይም ነሐስ በመቀነታችሁ አትያዙ፥ ለመንገዳችሁ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። በምትገቡባት በማንኛዪቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የተገባው ሰው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ወደ ቤቱም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱ የተገባው ከሆነ ሰላማችሁ በእርሱ ላይ ይሁን፤ ያልተገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ። ማንም የማይቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የማይሰማ ከሆነ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉችሁ ውጡ። እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል። “እነሆ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ። ከሰዎች ተጠንቀቁ፥ ምክንያቱም ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና፤ ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዢዎችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ። አሳልፈው በሰጡአችሁ ጊዜ፥ እንዴት ወይም ምን እንደምትናገሩ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና፤ በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና። ወንድም ወንድሙን፥ አባት ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸዋልም። ስለ ስሜ በሁሉም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ከዚያች ከተማ ቢያሳድዱአችሁ ወደ ሌላዪቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞች አትጨርሱም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች