ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ ራሱ ጠርቶ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ደዌንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው። የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፤ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣ ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ፣ ቀነናዊው ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ እንዲህ ከሚል ትእዛዝ ጋራ ላካቸው፤ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ። ይልቁንስ የእስራኤል ቤት ወደሆኑት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ። ሄዳችሁም፣ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ። በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ። “በመቀነታችሁ ወርቅም ሆነ ብር ወይም መዳብ አትያዙ። ለመንገዳችሁም ከረጢት፣ ትርፍ እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ የዕለት ጕርሱ ይገባዋልና። ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጋችሁ በቤቱ ዕረፉ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያው ቈዩ። ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ። ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስላችሁ። ማንም ሰው ሊያስተናግዳችሁ ወይም የምትናገሩትን ሊሰማ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከቤቱ ወይም ከከተማው ስትወጡ የእግሮቻችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ። እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። “እንግዲህ፣ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ። ሰዎች ይዘው ለፍርድ ወደ ሸንጎ ያቀርቧችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ከእነርሱ ተጠንቀቁ። በእኔ ምክንያት ወደ ገዦችና ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፤ በእነርሱና በአሕዛብም ፊት ምስክር ትሆናላችሁ። አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያ ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤ በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። “ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ አባትም ልጁን፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ያስገድሏቸዋልም። ስለ ስሜ ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል። በአንድ ስፍራ ሲያሳድዷችሁ ወደ ሌላ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የእስራኤልን ከተሞች ሳታዳርሱ የሰው ልጅ ይመጣል።
ማቴዎስ 10 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 10
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 10:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos