የሉቃስ ወንጌል 9:11-17

የሉቃስ ወንጌል 9:11-17 መቅካእኤ

ሕዝቡም ይህንን አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስም ያስፈልጋቸው የነበሩትንም ፈወሳቸው። ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ ዐሥራ ሁለቱም ቀርበው፦ “በዚህ በምድረ በዳ ስላለን በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት፤” አሉት። እርሱ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው፤” አላቸው። እነርሱም፦ “ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን በቀር ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም፤” አሉት፤ አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ፦ “በሃምሳ በሃምሳ እየከፈላችሁ አስቀምጡአቸው፤” አላቸው። እንዲህም አደረጉና ሁሉንም አስቀመጡአቸው። አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከእነርሱም የተረፈውን ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ።