የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 6:37-49

የሉቃስ ወንጌል 6:37-49 መቅካእኤ

“አትፍረዱ እንዳይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ እንዳትኰነኑም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ፤ ስጡ ይሰጣችኋልም፤ በመልካምም መስፈሪያ የተጠቀጠቀና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና።” እርሱም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ዐይነ ስውር ዐይነ ስውርን መምራት ይችላልን? ሁለቱም በጉድጓድ አይወድቁምን? ደቀመዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። በወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትም? አንተ ራስህ በዐይንህ ያለውን ምሰሶ ሳታይ እንዴት ወንድምህን፦ ‘ወንድሜ ሆይ! በዐይንህ ያለውን ጉድፍ እዳወጣ ፍቀድልኝ፤’ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።” መልካም ዛፍ የተበላሸ ፍሬ አያፈራምና፤ እንዲሁም የተበላሸ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፤ ከአጣጥ ቁጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። መልካም ሰው በልቡ ከሚገኘው መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሚገኘው ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል፤ በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና። ስለምን “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ትሉኛላችሁ? የምለውን ግን አታደርጉም? ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ፥ ቃሎቼንም ሰምቶ የሚያደርጋቸው ሰው ማንን እንደሚመስል አሳያችኋለሁ፤ እርሱም፦ ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ፥ በዐለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፤ ደኅና ተደርጎም ስለ ታነጸ ሊያናውጠው አልቻለም። ነገር ግን ሰምቶ የማያደርገው ቤቱን ያለ መሠረት በምድር ላይ የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው፤ ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።”