የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 4

4
የኢየሱስ መፈተን
(ማቴ. 4፥1-11ማር. 1፥12-13)
1ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በምድረ በዳም በመንፈስ ተመራ። 2ለአርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ። በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ ቀኖቹም በተፈጸሙ ጊዜ ተራበ። 3ዲያብሎስም፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ፤” አለው። 4#ዘዳ. 8፥3።ኢየሱስም፦ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ብሎ መለሰለት። 5ዲያብሎስም ከፍ ወዳለው ስፍራ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። 6ዲያብሎስም፦ “ለአንተ ይህን ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውንም እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥተቶአልና ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁ፤ 7ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤” አለው። 8#ዘዳ. 6፥13።ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤” አለው። 9ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቆመው፥ እንዲህም አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር፤ 10#መዝ. 90፥11፤12።እነሆ፥
‘አንተን ለመጠበቅ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤
11እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳይሰናከል
አንተን በእጃቸው ያነሡሃል፤’
ተብሎ ተጽፎአልና።” 12#ዘዳ. 6፥16።ኢየሱስም መልሶ፦ “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው፤’ ተብሏል፤” አለው። 13ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ከእርሱ ተለየ።
ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ መጀመሩ
(ማቴ. 4፥12-17ማር. 1፥14-15)
14ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለው አገር ሁሉ ተወራ። 15እንዲሁም በሁሉም እየተመሰገነ በምኵራባቸው ያስተምር ነበር።
16ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደተለመደው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ። 17የነቢዩም የኢሳይያስ ጥቅል ብራና ተሰጠው፤ ጥቅሉንም በዘረጋው ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ፤
18 # ኢሳ. 61፥1፤2። “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች
መልካም ዜናን እንዳበሥር ቀብቶኛልና፤
ለታሰሩትም መፈታትን ለዐይነ ስውሮችም ማየትን
እንዳውጅ፥ የተጨቆኑትንም ነጻ እንዳወጣ
19የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።”
20ጥቅል ብራናውንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ከሰጠ በኋላ ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር። 21እርሱም፦ “ዛሬ ይህ በጆሮዎቻችሁ የሰማችሁት ጽሑፍ ተፈጸመ፤” ይላቸው ጀመር። 22ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር፤ ከአፉም ከሚወጡት ቃላት ጸጋ የተነሣ እየተደነቁ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር። 23እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ያለ ምንም ጥርጥር ይህንን ምሳሌ ትጠቅሱብኛላችሁ ‘አንተ ሐኪም! እስቲ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግህ የሰማናቸውን ነገሮች ሁሉ፥ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ።’ ” 24#ዮሐ. 4፥44።እንዲህም አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፤ አንድም ነቢይ በገዛ አገሩ ተቀባይነት የለውም። 25#1ነገ. 17፥1።ነገር ግን በእውነት እላችኋለሁ፤ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ፥ በምድር ሁሉ ላይ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ 26#1ነገ. 17፥8-16።ቢሆንም ግን ኤልያስ ወደ ሲዶናዊቷ መበለት ወደ ሰራፕታ እንጂ ወደ ሌሎቹ ወደ አንዳቸውም አልተላከም። 27#2ነገ. 5፥1-14።በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ ማንም አልነጻም።” 28በምኵራብም ውስጥ የነበሩ ሁሉ እነዚህን ነገሮች በሰሙ ጊዜ በቁጣ ተሞሉ፤ 29ተነሥተውም ከከተማይቱ ውጭ አወጡት፤ ገፍትረውም ሊጥሉት ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ኮረብታ አፋፍ ላይ ወሰዱት፤ 30እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን ሰው መፈወሱ
(ማር. 1፥21-28)
31የገሊላ ከተማም ወደ ሆነችው ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤ 32#ማቴ. 7፥28፤29።ቃሉ በሥልጣን ተሞልቶ ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ። 33በምኵራብም የርኩስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፤ በታላቅ ድምፅም ጮኾ፦ 34“ተው፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደሆንህ አውቄሃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ፤” አለ። 35ኢየሱስም፦ “ዝም በል፤ ከእርሱም ውጣ፤” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ምንም ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ። 36ሁሉም ተደነቁ፤ እርስ በርሳቸውም፦ “ይህ ቃል ምንድነው? በሥልጣንና በኃይል ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፥ እነርሱም ይወጣሉ፤” እያሉ ይነጋገረሩ ነበር። 37ስለ እርሱም የተነገረው በዙሪያው ባለው አገር፥ በሁሉ ስፍራ ተሰራጭቶ ነበር።
ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት እና ብዙ ሕመምተኞችን መፈወሱ
(ማቴ. 8፥14-17ማር. 1፥29-34)
38ከምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ትኩሳት ታማ ነበር፤ ስለ እርሷም ለመኑት። 39በአጠገብዋም ቆሞ ትኩሳቱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ወዲያውም ተነሥታ አገለገለቻቸው። 40ፀሐይም ስትጠልቅ ሰዎች በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙባቸውን ሕሙማን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። 41አጋንንትም ደግሞ፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” ብለው እየጮኹ ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ እርሱ ግን ገሠጻቸው፤ እንዲናገሩም አልፈቀደላቸውም፥ ምክንያቱም ክርስቶስ እንደሆነ አውቀውት ነበርና።
42ሲነጋም ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፤ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ይጥሩ ነበር። 43እርሱ ግን፦ “የተላክሁት በዚሀ ምክንያት ነውና ለሌሎቹ ከተማዎችም የእግዚአብሔርን መንግሥት መልካም ዜና ማብሠር ይገባኛል፤” አላቸው። 44እርሱም በይሁዳ በሚገኙት ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ