የሉቃስ ወንጌል 18:15-43

የሉቃስ ወንጌል 18:15-43 መቅካእኤ

እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው። ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ተዉአቸው፤ አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም፤” አለ። ከአለቆችም አንዱ “ቸር መምህር! የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “ስለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛቱን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤” አለው። እርሱም “ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤” አለ። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ “አንዲት ነገር ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ፤” አለው። እርሱ ግን እጅግ ሀብታም ነበርና ይህንን ሰምቶ በጣም አዘነ። ኢየሱስም በዛም እንዳዘነ አይቶ “ሀብት ላላቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል። ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል፤” አለ። የሰሙትም “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። እርሱ ግን “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል፤” አለ። ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተለንሃል፤” አለ። እርሱም “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን፥ ሚስትን፥ ወንድሞችን፥ ወላጆችን ወይም ልጆችን የተወ፥ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም፤” አላቸው። ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል። ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፤ ያፌዙበታልም፤ ያንገላቱትማል፤ ይተፉበትማል፤ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።” እነርሱም ከዚህ ነገር ምንም አላስተዋሉም፤ ይህም ንግግር ተሰውሮባቸው ነበር፤ የተናገረውንም አላወቁም። ወደ ኢያሪኮም በቀረበ ጊዜ አንድ ዐይነ ስውር በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። ብዙ ሰዎች ሲያልፉ ሰምቶ “ይህ ምንድነው?” ብሎ ጠየቀ። እነርሱም “የናዝሬቱ ኢየሱስ እያለፈ ነው፤” ብለው አወሩለት። እርሱም “የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ! ማረኝ፤” እያለ ጮኸ። በስተ ፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ! ማረኝ፤” እያለ አብዝቶ ጮኸ። ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “ጌታ ሆይ! እንደገና ማየት እንድችል አድርገኝ፤” አለው። ኢየሱስም “እይ! እምነትህ አድኖሃል፤” አለው። በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም እያወደሰ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ ይህን አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።