የሉቃስ ወንጌል 18
18
የመበለትዋ እና የዐመፀኛው ዳኛ ምሳሌ
1ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንደሚገባቸው የሚያስተምር ምሳሌን ነገራቸው፤ 2እንዲህም አለ፦ “በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። 3በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፤ ወደ እርሱም እየመጣች ‘በባላጋራዬ ፊት ፍረድን ስጠኝ፤’ ትለው ነበር። 4ለአያሌ ቀናትም ሊፈርድላት አልፈለገም ነበር፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥ 5ይህች መበለት ስለምታደክመኝ፥ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ፤’ አለ።” 6ጌታም አለ፦ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። 7#ሲራ. 35፥19።እግዚአብሔር ታዲያ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ፥ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? 8ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል እላችኋለሁ። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?”
የፈሪሳዊው እና የቀራጩ ምሳሌ
9ጻድቃን ነን በማለት በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ 10እንዲህም አለ፦ “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፤ አንዱ ፈሪሳዊ ሌላውም ቀራጭ ነበር። 11ፈሪሳዊው ቆሞ እንዲህ ሲል በልቡ ጸለየ፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ! እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፥ ቀማኛና ዐመፀኛ አመንዝራም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ 12በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት እሰጣለሁ፤’ አለ። 13#መዝ. 51፥3።ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳን አልፈለገም፤ ነገር ግን ‘አምላክ ሆይ! እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ፤’ እያለ ደረቱን ይመታ ነበር። 14#ማቴ. 23፥12፤ ሉቃ. 14፥11።ከዚያኛው ይልቅ ይህ ሰው ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ እላችኋለሁ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፥ ራሱን ግን ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል።”
ኢየሱስ ሕፃናትን እንደ ባረከ
(ማቴ. 19፥13-15፤ ማር. 10፥13-16)
15እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው። 16ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ተዉአቸው፤ አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 17እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም፤” አለ።
የሀብታሙ ገዥ ጥያቄ
(ማቴ. 19፥16-30፤ ማር. 10፥17-31)
18ከአለቆችም አንዱ “ቸር መምህር! የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው። 19ኢየሱስም “ስለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። 20#ዘፀ. 20፥14፤ ዘዳ. 5፥18፤ ዘፀ. 20፥13፤ ዘዳ. 5፥17፤ ዘፀ. 20፥15፤ ዘዳ. 5፥19፤ ዘፀ. 20፥16፤ ዘዳ. 5፥20፤ ዘፀ. 20፥12፤ ዘዳ. 5፥16።ትእዛዛቱን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤” አለው። 21እርሱም “ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤” አለ። 22ኢየሱስም ይህን ሰምቶ “አንዲት ነገር ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ፤” አለው። 23እርሱ ግን እጅግ ሀብታም ነበርና ይህንን ሰምቶ በጣም አዘነ። 24ኢየሱስም በዛም እንዳዘነ አይቶ “ሀብት ላላቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል። 25ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል፤” አለ። 26የሰሙትም “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። 27እርሱ ግን “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል፤” አለ። 28ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተለንሃል፤” አለ። 29እርሱም “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን፥ ሚስትን፥ ወንድሞችን፥ ወላጆችን ወይም ልጆችን የተወ፥ 30በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም፤” አላቸው።
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለሦስተኛ ጊዜ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 20፥17-19፤ ማር. 10፥32-34)
31ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል። 32ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፤ ያፌዙበታልም፤ ያንገላቱትማል፤ ይተፉበትማል፤ 33ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።” 34እነርሱም ከዚህ ነገር ምንም አላስተዋሉም፤ ይህም ንግግር ተሰውሮባቸው ነበር፤ የተናገረውንም አላወቁም።
ኢየሱስ በኢያሪኮ አንድ ዐይነ ስውር እንደ ፈወሰ
(ማቴ. 20፥29-34፤ ማር. 10፥46-52)
35ወደ ኢያሪኮም በቀረበ ጊዜ አንድ ዐይነ ስውር በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 36ብዙ ሰዎች ሲያልፉ ሰምቶ “ይህ ምንድነው?” ብሎ ጠየቀ። 37እነርሱም “የናዝሬቱ ኢየሱስ እያለፈ ነው፤” ብለው አወሩለት። 38እርሱም “የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ! ማረኝ፤” እያለ ጮኸ። 39በስተ ፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ! ማረኝ፤” እያለ አብዝቶ ጮኸ። 40ኢየሱስም ቆመና ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። 41እርሱም “ጌታ ሆይ! እንደገና ማየት እንድችል አድርገኝ፤” አለው። 42ኢየሱስም “እይ! እምነትህ አድኖሃል፤” አለው። 43በዚያን ጊዜም አየ፤ እግዚአብሔርንም እያወደሰ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ ይህን አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 18: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ