የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 13

13
ንስሓ የማይገባ ሁሉ ይጠፋል
1በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት። 2ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በእነዚህ የገሊላ ሰዎች ላይ ይህ የደረሰው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኀጢአተኞች ስለ ሆኑ ይመስላችኋልን?” 3“አይደለም”፤ እላችኋለሁ፥ “ነገር ግን ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁም እንዲሁ ትጠፋላችሁ። 4ወይንስ በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ 5ነገር ግን ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁም እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።”
የማታፈራ የበለስ ዛፍ ምሳሌ
6ይህንንም ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው በወይን አትክልቱ ቦታ የተተከለች በለስ ነበረችው፤ በእርሷም ፍሬ ፈልጎ ቢመጣ ምንም አላገኘም። 7የወይን አትክልት ሠራተኛውንም ‘እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ፈልጌ ለሦስት ዓመት ብመላለስ ምንም አላገኘሁም፤ ቁረጣት፤ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቁላለች?’ አለው። 8እርሱ ግን መልሶ፥ ጌታ ሆይ! ዙሪያዋን እስክኰተኩትላትና ፍግ እስካፈስላት ድረስ ይህችን ዓመት ደግሞ ተዋት። 9ወደፊትም ብታፈራ፥ መልካም ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ” አለው።
ኢየሱስ በሰንበት አንዲት ጎባጣ ሴት እንደ ፈወሰ
10በሰንበት ቀንም ከምኵራቦቹ በአንዱ ያስተምር ነበር። 11እነሆም፥ ከዐሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ርኩስ መንፈስ በሽተኛ ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ጎባጣ ነበረች፤ ቀጥ ብላ መቆምም በፍጹም አልተቻላትም። 12ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት! ከበሽታሽ ተፈውሰሻል፤” አላት፤ 13እጁንም ጫነባት፤ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። 14#ዘፀ. 20፥9፤10፤ ዘዳ. 5፥13፤14።የምኵራብ አለቃው ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ ሕዝቡን “ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይሆንም፤” አለ። 15ጌታም መልሶ እናንተ ግብዞች! ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውሃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? 16ይህች ለዐሥራ ስምንት ዓመት ሰይጣን ያሠራት የአብርሃም ልጅ በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። 17ይህንንም ሲናገር የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ በእርሱም በተደረጉት ድንቅ ነገሮች ሁሉ ሕዝቡ በሙሉ ደስ አለው።
ስለ ሰናፍጭ ዘር እና ስለ እርሾ ምሳሌ
(ማቴ. 13፥31-33ማር. 4፥30-32)
18እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ምንን ትመስላለች? በምንስ እመስላታለሁ? 19ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤እርሷም አደገች፤ ታላቅ ዛፍም ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ፤”።
20ደግሞም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ? 21አንዲት ሴት ወስዳ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች፤” አለ።
ስለ ጠባብዋ በር
(ማቴ. 7፥13-1421-23)
22ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ ከተማዎችንና መንደሮችን እያስተማረ ያልፍ ነበር። 23አንድ ሰውም “ጌታ ሆይ! የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ 24“በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ፥ አይችሉምም እላችኋለሁ። 25ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም መልሶ ‘ከየት እንደ ሆናችሁ አላውቅም’ ይላችኋል። 26በዚያን ጊዜም ‘በፊትህ በላን፤ ጠጣንም፤ በአደባባያችንም አስተማርህ፤’ ማለት ትጀምራላችሁ፤ 27#መዝ. 6፥8።እርሱም ‘እላችኋለሁ፥ ከየት እንደ ሆናችሁ አላወቅም፤ ዐመፀኞች በሙሉ፥ ከእኔ ራቁ፤’ ይላችኋል። 28#ማቴ. 22፥13፤ 25፥30።#ማቴ. 8፥11፤12።አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን፥ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት እያያችሁ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 29ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ። 30#ማቴ. 19፥30፤ 20፥16፤ ማር. 10፥31።እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፤ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”
ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን እንደ ወቀሰ
(ማቴ. 23፥37-39)
31በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዶች ቀርበው “ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ውጣና ሂድ፤” አሉት። 32እንዲህም አላቸው “ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ ‘እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን እፈጽማለሁ’ በሉአት። 33ዳሩ ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ሊጠፋ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ በስቲያም መሄድ ያስፈልገኛል። 34#19፥41-44፤ ማቴ. 23፥37-39።ኢየሩሳሌም! ኢየሩሳሌም! ነቢያትን የምትገድል፥ ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ፤ እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። 35#19፥38፤ 1ነገ. 9፥7-8፤ መዝ. 118፥26፤ ኤር. 7፥4-7፤13-15፤ 12፥7፤ 22፥5።እነሆ፥ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል። በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም እላችኋለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ