ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣትዋ እንዴት ያለ ነገር ነው? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ ወደ ጆሮዬ በደረሰ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸም ያመነች ምንኛ ብፅዕት ናት።” ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ እኔን ዝቅተኛይቱን አገልጋይ ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ሁሉን የሚችል እርሱ ለእኔ ታላላቅ ነገሮችን አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ በሚፈሩት ላይ ይኖራል። በክንዱ ኃያል ሥራን ሠርቶአል፤ በልባቸው የሚታበዩትን በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ሀብታሞችን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። እስራኤልን አገልጋዩን፥ ምሕረቱን በማስታወስ፥ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም እንደ ተናገረው ረድቶአል።” ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርሷ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚያም ወደ ቤትዋ ተመለሰች። የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርሷ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። እናቱ ግን መልሳ፦ “እንዲህ አይሆንም፤ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራ እንጂ፤” አለች። እነርሱም፦ “ከዘመዶችሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም፤” አሉአት። ማን ተብሎ ቢጠራ እንደሚወድ አባቱንም በምልክት ጠየቁ። ሰሌዳም ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው፤” ብሎ ጻፈ። ሁሉም ተደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ተናገረ። በጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ላይ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በተራራማው በይሁዳ አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ በእርግጥ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትንቢት ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፤ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፥ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንዲሁም ለአባቶቻችን ምሕረትን አደረገ፤ ቅዱስ ኪዳኑንም ለአባታችን ለአብርሃም በመሐላ እንደማለለት አስታወሰ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሃት በዘመናችን ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ለማዘጋጀት በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንዲሁም በኀጢአታቸው ስርየት የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ በአምላካችን የርኅራኄ ምሕረት ከላይ የሚመጣው ብርሃን ይጐበኘናልና፤ እርሱም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።” ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:40-80
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች