የሉቃስ ወንጌል 1:1-56

የሉቃስ ወንጌል 1:1-56 መቅካእኤ

እጅግ የተከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ብዙዎች በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ክስተቶች በጽሑፍ ለማዘጋጀት እንደሞከሩት ሁሉ፥ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት ለእኛ ባስተላለፉልን መሠረት፥ ከመጀመሪያው አንሥቶ ስለሆኑት ነገሮች ሁሉ በጥንቃቄ በመመርመር፥ ለአንተ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ታሪክ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ። በዚህም ስለ ተማርካቸው ነገሮች እርግጠኛነት በደንብ እንድታውቅ ብዬ ነው። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ሴት ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በጌታ ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ ይመላለሱ ነበር። ኤልሳቤጥም መካን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት ሲያገለግል፥ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጀን ሕዝብ ለጌታ አሰናድቶ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ለመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፦ “እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለችና ይህንን በምን አውቃለሁ?” አለው። መልአኩም መልሶ፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድነግርህም ይህችንም የምሥራች እንዳበሥርህ ተልኬአለሁ፤ እነሆም፥ በጊዜያቸው የሚፈጸሙትን ቃሎቼን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆንበት ቀን ድረስ አንደበትህ ይታሰራል፤ መናገርም አትችልም፤” አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመዘግየቱም ተገረሙ። በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ፤ እርሱም በምልክት ያናግራቸው ነበር፤ ዲዳም ሆኖ ቆየ። የአገልግሎቱም ጊዜ እንደ ተፈጸመ ወደ ቤቱ ሄደ። ከነዚያም ቀኖች በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወር ተደበቀች፤ እንዲህም አለች፦ “ጌታ እኔን በተመለከተበት ጊዜ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል አስወገደልኝ።” በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል በገሊላ ወደምትገኝ ከተማ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።፥ የተላከውም ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ገብቶ፦ “ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤” አላት። እርሷም በንግግሩ በጣም ደንግጣ፥ “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” ማርያምም መልአኩን፦ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለችው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርሷ ደግሞ በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን ትባል ለነበረችው ለእርሷም ይህ ስድስተኛ ወሯ ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው አንዳች ነገር የለምና።” ማርያምም፦ “እነሆኝ የጌታ አገልጋይ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፤” አለች። መልአኩም ከእርሷ ተለይቶ ሄደ። ማርያምም በእነዚያ ቀናት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር በይሁዳ ወደምትገኝ ከተማ ፈጥና ሄደች፤ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣትዋ እንዴት ያለ ነገር ነው? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ ወደ ጆሮዬ በደረሰ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸም ያመነች ምንኛ ብፅዕት ናት።” ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ እኔን ዝቅተኛይቱን አገልጋይ ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ሁሉን የሚችል እርሱ ለእኔ ታላላቅ ነገሮችን አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ በሚፈሩት ላይ ይኖራል። በክንዱ ኃያል ሥራን ሠርቶአል፤ በልባቸው የሚታበዩትን በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ሀብታሞችን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። እስራኤልን አገልጋዩን፥ ምሕረቱን በማስታወስ፥ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም እንደ ተናገረው ረድቶአል።” ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርሷ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚያም ወደ ቤትዋ ተመለሰች።