የተከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ በእኛ መካከል የተፈጸሙትን ነገሮች የሚገልጥ ታሪክ ከዚህ ቀደም ብዙዎች ጽፈዋል። ይህን መልእክት ለእኛ ያስተላለፉልን ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ናቸው። እንዲሁም እኔ ከመጀመሪያው አንሥቼ ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ከመረመርኩ በኋላ ታሪኩን በቅደም ተከተል እጽፍልህ ዘንድ መልካም ሆኖ አገኘሁት። ይህንንም ማድረጌ የተማርከውን ትምህርት እውነተኛነት በደምብ እንድትረዳ ብዬ ነው። ሄሮድስ በይሁዳ ምድር ንጉሥ በነበረበት ዘመን፥ ከአብያ የክህነት አገልግሎት ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል ካህን ነበር። እርሱም ከአሮን ዘር የምትወለድ ኤልሳቤጥ የምትባል ሚስት ነበረችው። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ የጌታንም ትእዛዝና ሥርዓት ያለ ነቀፋ ይጠብቁ ነበር። ኤልሳቤጥ መኻን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ደግሞ ሁለቱም በጣም አርጅተው ነበር። በዚያን ጊዜ የዘካርያስ የክህነት ቡድን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ተረኛ ነበር፤ ስለዚህ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት የክህነቱን አገልግሎት በመፈጸም ላይ ነበር። እንደ ካህናት አሠራር ልማድ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዕጣን በሚታጠንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ በውጪ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታ መልአክ ዕጣን በሚጤስበት መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ለዘካርያስ ታየው። ዘካርያስ መልአኩን ባየው ጊዜ ደንግጦ በፍርሃት ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! አትፍራ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። የእርሱ መወለድ ለአንተ ተድላና ደስታ ይሆንልሃል፤ ብዙዎችም በመወለዱ እንዲሁ ደስ ይላቸዋል። እርሱ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናል፤ የወይን ጠጅና ሌላም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገና በእናቱ ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል። እርሱ ከእስራኤል ሕዝብ ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ ልክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ በመንፈስና በኀይል ሆኖ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፥ የማይታዘዙትንም ሰዎች ልብ ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልሳል፤ ሕዝቡንም በማንቃት ለጌታ እንዲዘጋጅ ያደርጋል።” ዘካርያስ ግን መልአኩን “ይህ ነገር እርግጥ መሆኑን በምን ዐውቃለሁ? እኔ አርጅቻለሁ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለች” አለው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን የምሥራች እንድነግርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬ መጥቻለሁ። አንተ ግን ጊዜው ሲደርስ የሚፈጸመውን ቃሌን አላመንክም፤ ስለዚህ ይህ የነገርኩህ ሁሉ እስከሚፈጸም ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።” በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ዘካርያስን ይጠባበቁ ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ስለ ዘገየባቸውም ተገረሙ። ዘካርያስ ከቤተ መቅደስ በወጣ ጊዜ ከሰዎቹ ጋር መነጋገር አልቻለም፤ ስለዚህ እነርሱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ራእይ የታየው መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ በእጁ እየጠቀሰ ያስረዳቸው ነበር። በዚህም ሁኔታ ዱዳ ሆኖ ቈየ። የአገልግሎቱም ጊዜ ከተፈጸመ በኋላ ዘካርያስ ወደ ቤቱ ሄደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወር በቤትዋ ውስጥ ተሸሽጋ ቈየች፤ እንዲህም አለች፦ “ጌታ ይህን መልካም ነገር አደረገልኝ፤ በሰዎች መካከል የነበረብኝን ነቀፌታ አስወገደልኝ።” ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል በገሊላ ምድር ወደምትገኝ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ ከእግዚአብሔር ተላከ። የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር። መልአኩም ወደ እርስዋ መጥቶ፦ “አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፥ ሰላም ለአንቺ ይሁን! ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ [አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ]” አላት። እርስዋም በመልአኩ አነጋገር በጣም ደንግጣ፥ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ፤ እነሆ! ትፀንሺአለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። በእስራኤልም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” ማርያም መልአኩን “እኔ ድንግል ነኝ፤ ታዲያ፥ ይህ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል እግዚአብሔርም ኀይል በአንቺ ላይ ይሆናል፤ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ሕፃን ቅዱስ ነው፤ የእግዚአብሔርም ልጅ ይባላል። ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እንኳ መኻን ስትባል ኖራ አሁን በስተእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ ከፀነሰችም እነሆ፥ ስድስተኛ ወርዋ ነው። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም።” ከዚያም በኋላ ማርያም፥ “እነሆ! እኔ የጌታ አገልጋይ ነኝ፤ አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ” አለችው። በዚህ ጊዜ መልአኩ ተለይቶአት ሄደ። በዚያን ጊዜ ማርያም በተራራማው በይሁዳ አገር ወዳለችው ከተማ በፍጥነት ተነሥታ ሄደች። ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥ የማርያምን የሰላምታ ቃል በሰማች ጊዜ በማሕፀንዋ የነበረው ሕፃን ዘለለ። ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ ድምፅዋንም ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ ከአንቺ የሚወለደውም የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ልትጐበኘኝ መምጣትዋ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው፤ ገና የሰላምታሽን ድምፅ ከመስማቴ በማሕፀኔ ያለው ሕፃን በደስታ ዘለለ። አንቺ ጌታ የተናገረውን ሁሉ የሚፈጽም መሆኑን በማመንሽ ምንኛ የተባረክሽ ነሽ!” ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታመሰግናለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ትደሰታለች፤ እግዚአብሔር እኔን ዝቅተኛ አገልጋይቱን ተመልክቶአልና፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ የተባረክሽ ነሽ ይሉኛል፤ ኀያሉ እግዚአብሔር ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልኛልና። ስሙም ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር ለሚፈሩት ሰዎች ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ምሕረቱን ያደርጋል። በብርቱ ክንዱ ኀይሉን አሳይቶአል፤ ትዕቢተኞችንም ከነሐሳባቸው በትኖአቸዋል። ታላላቅ ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤ ዝቅተኞችን ግን በክብር ከፍ አድርጎአቸዋል። የተራቡትን በመልካም ነገር አጥግቦአቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዶ እጃቸውን ሰዶአቸዋል፤ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም ያሳየውን ምሕረት በማስታወስ፥ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቶታል። ይህንንም ያደረገው ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ነው።” ማርያምም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያኽል ከቈየች በኋላ ወደ ቤትዋ ተመልሳ ሄደች።
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:1-56
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos