ኦሪት ዘሌዋውያን 9
9
አሮን የክህነት አገልግሎቱን መጀመሩ
1 #
ዘሌ. 8፥33። በስምንተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አሮንንና ልጆቹን የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ጠራ። 2አሮንንም እንዲህ አለው፦ “ከመንጋው ነውር የሌለባቸውን ለኃጢአት መሥዋዕት እምቦሳውን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አውራውን በግ ወስደህ በጌታ ፊት አቅርብ። 3ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፦ ‘ለኃጢአት መሥዋዕት አውራ ፍየልን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን አንድ ዓመት የሆናቸውን እምቦሳና ጠቦትን፥ 4ለአንድነትም መሥዋዕት በሬንና አውራን በግ፥ በዘይትም የተለወሰ የእህልን ቁርባን በጌታ ፊት ለመሠዋት ውሰዱ፥ ዛሬ ጌታ ተገልጦላችኋልና።’ ” 5ሙሴም ያዘዛቸውን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ማኅበሩም ሁሉ ቀርበው በጌታ ፊት ቆሙ። 6ሙሴም፦ “የጌታም ክብር እንዲገለጥላችሁ ጌታ እንድታደርጉት ያዘዘው ይህን ነገር ነው፤” አለ። 7#ዘሌ. 16፥3-5።ሙሴም አሮንን፦ “ወደ መሠዊያው ቅረብ፥ የኃጢአትህንም መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፥ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ ጌታም እንዳዘዘ የሕዝቡን ቁርባን አቅርብ አስተስርይላቸውም” አለው።
8አሮንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ ኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን እምቦሳ አረደ። 9#ዘሌ. 4፥25፤30፤34።የአሮንም ልጆች ደሙን አቀረቡለት፤ ጣቱንም በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፥ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው። 10ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው ከኃጢአቱ መሥዋዕት ስቡንና ኩላሊቶቹን፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 11#ዘሌ. 6፥23።ሥጋውንና ቆዳውንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ።
12የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ እርሱም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ረጨው። 13በየብልቱም የተሸነሸነውን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ከጭንቅላቱ ጋር አመጡለት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 14#ዘሌ. 1፥5-9።የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም አጠበ፤ በመሠዊያውም ባለው የሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው።
15ከዚያም በኋላ የሕዝቡን ቁርባን አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ አረደው፥ ስለ ኃጢአትም እንደ ፊተኛው የኃጢአት መሥዋዕት ሠዋው። 16እንደ ሥርዓቱም አድርጎ የሚቃጠለውን መሥዋዕትም አቀረበ። 17#ዘኍ. 28፥23፤ 2ነገ. 16፥15፤ ሕዝ. 46፥13-15።የእህሉንም ቁርባን አቀረበ፥ ከእርሱም እፍኝ ሙሉ ወስዶ በጥዋት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት አጠገብ በመሰዊያው ላይ አቃጠለው።
18 #
ዘሌ. 3፥2። ስለ ሕዝቡ የአንድነት መሥዋዕት የሚቀርበውን በሬውንና አውራውን በግ አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ በመሠዊያውም ላይ በዙሪያው ረጨው፤ 19የበሬውንና የአውራውንም በግ ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ ኩላሊቶቹንም፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ አመጡለት። 20ስቡንም በፍርምባዎቹ ላይ አደረጉ፥ እርሱም ስቡን በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ 21#ዘሌ. 7፥30-34።ሙሴም እንደ ታዘዘው አሮን ፍርምባዎቹንና ቀኝ ወርቹን በጌታ ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዘ።
22 #
ዘኍ. 6፥22-27። አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም፤ እርሱም የኃጢአቱንና የሚቃጠለውን የሰላሙንም መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ ወረደ። 23ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ በወጡም ጊዜ ሕዝቡን ባረኩ፤ የጌታም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። 24#1ነገ. 18፥38፤ 2ዜ.መ. 7፥1፤ 2መቃ. 2፥10፤ ዘፀ. 24፥16-17።እሳትም ከጌታ ዘንድ ወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እልል አሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ሰገዱ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ