“እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝና ለራሳችሁ ይሆኑ ዘንድ ጣዖታትን አትሥሩ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ለእርሱም ለመስገድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ። ሰንበታቴን ጠብቁ፥ ለመቅደሴም ክብርን ስጡ፤ እኔ ጌታ ነኝ። “በሥርዓቶቼ ብትመላለሱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉአቸውም፥ ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም የተትረፈረፈ ምርትዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። ለእናተም እህሉን ማበራየቱ የወይኑን ዘለላ እስከሚቆረጥበት ወቅት ድረስ ይደርሳል፥ የወይኑንም ዘለላ መቁረጥ እህል እስከ ሚዘራበት ወቅት ድረስ ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። በምድሪቱም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራራችሁ ያለ ስጋት ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በእናንተም ፊት በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም ዓሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በእናንተ ፊት በሰይፍ ይወድቃሉ። ወደ እናንተም ዘወር ብዬ በበጎ እመለከታችኋለሁ፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። ለብዙም ጊዜ በጎተራ የተቀመጠውን ቀድሞ የነበረውን እህል ትበላላችሁ፤ ለአዲሱም ቦታ ለማስለቀቅ ቀድሞ በጎተራ የነበረውን ታወጣላችሁ። ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እመላለሳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። ባርያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁም እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።” ጌታም እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን እኔን ባትሰሙና እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ ሥርዓቴንም ባትቀበሉ፥ ነፍሳችሁም ፍርዴን በመጸየፉዋ ምክንያት ትእዛዛቴን ሳታደርጉ ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፥ እኔ ደግሞ እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ነፍስን የሚያኮስስና ዓይንን የሚያፈዝዝ ክሳትና ትኩሳት አመጣባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁም ይበሉታልና ዘራችሁን በከንቱ ትዘራላችሁ። ፊቴንም አጠቊርባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትሸነፋላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። እነዚህም ነገሮች ተደርገውባችሁ እንኳ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ ጨምሬ ዳግመኛ እቀጣችኋለሁ። የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። ጉልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም የተትረፈረፈውን ምርትዋን አትሰጥም፥ የምድሪቱም ዛፎች ፍሬያቸውን አይሰጡም። “እኔንም በመቃወም ብትሄዱ ልትሰሙኝም ባትፈልጉ፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን ሰባት እጥፍ ቸነፈር እጨምርባችኋለሁ። በመካከላችሁም የዱር አራዊትን እለቅባችኋለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይነጥቁአችኋል፥ እንሰሶቻችሁንም ያጠፉባችኋል፥ እናንተንም ቁጥራችሁን ያመነምኑታል፤ መንገዶቻችሁም የተራቈቱ ይሆናሉ። “በእነዚህም ተቀጥታችሁ ወደ እኔ ባትመለሱ፥ ይልቁንም እኔን በመቃወም ብትሄዱ፥ እኔም ደግሞ እናንተን በመቃወም እሄዳለሁ፤ እኔም ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። የቃል ኪዳኑንም በቀል የሚበቀል ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተሞቻችሁም ትሰበሰባላችሁ፥ በመካከላችሁም ቸነፈርን እልክባችኋለሁ፤ በጠላትም እጅ ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ። የእንጀራችሁንም በትር በሰበርሁ ጊዜ፥ ዐሥር ሴቶች እንጀራችሁን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው ዳግመኛ እንጀራችሁን ያመጡላችኋል፤ ትበላላችሁም ነገር ግን አትጠግቡም።
ኦሪት ዘሌዋውያን 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 26:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች