ኦሪት ዘሌዋውያን 18
18
ስለ ግብረ ሥጋ ግንኙነት
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። 3#ዘሌ. 20፥22-23።በተቀመጣችሁባት በግብጽ ምድር እንደሚያደርጉት እናንተም እንዲሁ አታድርጉ፤ እኔም ወደማመጣችሁ ስፍራ ወደ ሆነው በከነዓን ምድር ላይ እንደሚያደርጉት እናንተም እንዲሁ አታድርጉ፤ በሥርዓታቸውም አትሂዱ። 4ፍርዴን ፈጽሙ፥ ሥርዓቴንም ጠብቁ፥ በእነርሱም ተመላለሱ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ። 5#ሕዝ. 20፥11፤ 13፤ 21፤ ገላ. 3፥12።ስለዚህ ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፥ እነርሱን የሚያደርግ ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና፤ እኔ ጌታ ነኝ።
6“ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ለመግለጥ ወደ ሥጋ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ ጌታ ነኝ። 7#ዘሌ. 20፥11፤ ዘዳ. 23፥1፤ 27፥20፤ 1ቆሮ. 5፥1።የአባትህ ኃፍረተ ሥጋ ነውና የእናትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እናትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 8የአባትህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ኃፍረተ ሥጋ ነው። 9#ዘሌ. 20፥17፤ ዘዳ. 27፥22።የእኅትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የእናትህ ልጅ፥ በአገር ቤት ወይም በውጭ አገር የተወለደች ብትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 10የወንድ ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ወይም የሴት ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ፤ የእነርሱ ኃፍረተ ሥጋ የአንተ ኃፍረተ ሥጋ ነውና። 11#ዘሌ. 20፥17።እርሷ እኅትህ ነችና ከአባትህ የተወለደችውን የአባትህን ሚስት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 12#ዘሌ. 20፥19።የአባትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ዘመድ ናት። 13የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የእናትህ ዘመድ ናትና። 14#ዘሌ. 20፥20።የአባትህን ወንድም ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፥ ወደ ሚስቱም አትቅረብ፤ የአጎትህ ሚስት ናት፤ 15#ዘሌ. 20፥12።የምራትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 16#ዘሌ. 20፥21፤ ዘዳ. 25፥5-10፤ ማቴ. 14፥3-4፤ ማር. 6፥18።የወንድምህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድምህ ኃፍረተ ሥጋ ነው። 17#ዘሌ. 20፥14፤ ዘዳ. 27፥23።የሴትንና የሴት ልጇን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድ ልጇን ሴት ልጅ ወይም የሴት ልጇን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ለመግለጥ እርሷን አታግባ፤ ዘመዶች ናቸው፤ ዝሙት ነው። 18#ዘፍ. 29፥27-28።እኅትዋ በሕይወት እስካለች ድረስ ኃፍረተ ሥጋዋን ለመግለጥ የእርሷን እኅት እንደ ሁለተኛ ሚስት አድርገህ አታግባ።
19 #
ዘሌ. 15፥24፤ 20፥18፤ ሕዝ. 18፥6፤ 22፥10። “እርሷም ርኩስ በሆነችበት የወር አበባዋ ጊዜያት ላይ ሳለች ኃፍረተ ሥጋዋን ለመግለጥ ወደ ሴት አትቅረብ። 20#ዘሌ. 20፥10፤ ዘፀ. 20፥14፤ ዘዳ. 5፥18፤ 22፥22፤ ማቴ. 5፥27-30፤ ዮሐ. 8፥4-5።በእርሷም ራስህን እንዳታረክስ ከባልንጀራህ ሚስት ጋር አትተኛ። 21#ዘሌ. 20፥2-5፤ ዘዳ. 18፥10፤ 1ነገ. 11፥7፤ 2ነገ. 16፥3።ከልጆችህ ማናቸውንም ለሞሌክ በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ አትስጥ፥ በዚህም የአምላክህን ስም አታርክስ፤ እኔ ጌታ ነኝ። 22#ዘሌ. 20፥13፤ ዘፍ. 19፥4-11፤ መሳ. 19፥22-30፤ ሮሜ 1፥27፤ 1ቆሮ. 6፥9።ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነው። 23#ዘሌ. 20፥15-16፤ ዘፀ. 22፥18፤ ዘዳ. 27፥21።በእርሱም ራስህን እንዳታረክስ ከማናቸውም እንሰሳ ጋር አትተኛ፤ ሴት ከእርሱ ጋር ለመተኛት በእንስሳ ፊት አትቁም፤ ጸያፍ የሆነ ተግባር ነው።
24“በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ራሳችሁን አታርክሱ። 25#ዘሌ. 20፥22።ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ስለ በደልዋ እቀጣታለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች አንቅራ ትተፋቸዋለች። 26ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩም ተወላጅ በእናንተም መካከል የሚኖር እንግዳ ርኩሰት ከሆኑት ከእነዚህ ማናቸውንም ነገር አታድርጉ፤ 27ከእናንተ በፊት የነበሩ የምድሪቱ ሰዎች ይህን ርኩሰት ሁሉ አድርገዋልና፥ ስለዚህ ምድሪቱ ረክሳለች፤ 28ያለዚያ ግን ምድሪቱን ካረከሳችሁ እርሷ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ አንቅራ እንደ ተፋች እንዲሁ እናንተንም አንቅራ ትተፋችኋለች። 29በእርግጥ ማንም ሰው ርኩሰት ከሆኑት ከእነዚህ ነገሮች ማናቸውንም ነገር ቢያደርግ፥ ያደረጋችው ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። 30#ዘሌ. 20፥23፤ ዘዳ. 18፥9።ስለዚህ ከእናንተ በፊት በምድሪቱ ላይ የተደረገውን ጸያፍ ወግ ሁሉ ፈጽሞ እንዳታደርጉ፥ በእርሱም ራሳችሁን ፈጽሞ እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 18: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ