ኦሪት ዘሌዋውያን 13

13
የሥጋ ደዌ ዓይነቶቹ እና ምልክቶቹ
1ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2#ዘሌ. 22፥4፤ ዘፀ. 4፥6፤ ዘኍ. 5፥2-3፤ ዘዳ. 24፥8፤ 2ሳሙ. 3፥29፤ 2ነገ. 5፥1፤ 3—7፤ 11፤ ማር. 1፥40-45።ማናቸውም ሰው በሰውነቱ ቆዳ ላይ እባጭ ወይም ብጉር ወይም ቋቁቻ ቢታይ፥ በሰውነቱ ቆዳ እንደ ለምጽ ደዌ ቢሆን፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ከልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። 3ካህኑም በሰውነቱ ቆዳ ላይ ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ከሰውነቱ ቆዳ በታች ዘልቆ ቢታይ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ፦ ርኩስ ነው ይበለው። 4ነገር ግን ቋቁቻው በሰውነቱ ቆዳ ላይ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ በእርሱም ላይ ያለው ጠጉር ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። 5በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው መገታቱን ቢያይ፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ፥ አሁንም ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። 6በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ዳግም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል። 7ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቆዳው ላይ ቢስፋፋ፥ እንደገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። 8ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው።
9ማናቸውም ሰው በለምጽ ደዌ ቢጠቃ እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡታል፤ 10ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቆዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢኖር፥ በእርሱም ላይ ያለውን ጠጉር ለውጦት ቢያነጣው፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ 11እርሱ በሰውነቱ ቆዳ ላይ የቈየ የለምጽ ደዌ ነው፥ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይለየውም። 12ለምጹም በቆዳው ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ካህኑ ማየት እስከሚችልበት አካል የለምጹ ደዌ የታመመውን ሰው ቆዳ ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ ቢሸፍነው፥ 13ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ሰውነቱን ሁሉ ቢሸፍነው የታመመውን ሰው፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሰውነቱ ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው። 14የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል። 15ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ የለምጽ ደዌ ነውና ርኩስ ነው። 16የሚያዠው ሥጋ ግን ተለውጦ ቢነጣ እንደገና ወደ ካህኑ ይመጣል። 17ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው።
18በሰውነቱም ቆዳ ላይ የዳነ የብጉንጅ ቁስል ቢኖር፥ 19በብጉንጁም የቁስል ስፍራ ላይ ነጭ እባጭ ወይም ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል። 20ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ቢታይ፥ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከብጉንጁ ቁስል ውስጥ ወጥቶአል። 21ካህኑም ቢያየው፥ እነሆም፥ በእርሱ ላይ ነጭ ጠጉር ባይኖርበት፥ ከቆዳውም በታች ባይዘልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። 22በቆዳውም ላይ ቢስፋፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው። 23ቋቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የብጉንጅ ቁስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። 24“በሰውነቱም ቆዳ ላይ የእሳት ቃጠሎ ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣበት፥ 25ካህኑ ያየዋል፥ እነሆም፥ በቋቁቻው ላይ ያለው ጠጉር ተለውጦ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ቢታይ፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። 26ነገር ግን ካህኑ ቢያየው፥ በቋቁቻውም ላይ ነጭ ጠጉር ባይኖር፥ ከቆዳውም በታች ባይዘልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። 27ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቆዳውም ላይ ቢስፋፋ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። 28ቋቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የቃጠሎው እባጭ ነው፤ የቃጠሎውም ጠባሳ ነውና ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል።
29“ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራስ ወይም በአገጭ ላይ ደዌ ቢኖርባቸው፥ 30ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ከቆዳው በታች ዘልቆ ቢታይ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጉር ቢኖርበት፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ የለምጽ ደዌ ነው። 31ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ ጥቁርም ጠጉር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። 32ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጉር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ከቆዳው በታች ባይዘልቅ፥ 33ይላጫል፥ ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ አሁንም ካህኑ ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። 34ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል። 35ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢስፋፋ፥ 36ካህኑ ያየዋል፤እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጉር አይፈልግም፤ እርሱ ርኩስ ነው። 37ቈረቈሩ ግን መገታቱን ቢያይ፥ ጥቁርም ጠጉር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ድኖአል፤ እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል።”
38“ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሰውነታቸው ቆዳ ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢኖርባቸው፥ 39ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሰውነታቸው ቆዳ ላይ ያለው ቋቁቻ ደብዘዝ ያለ ነጭ ቢሆን በቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ነው፤ ከቆዳው ውስጥ ወጥቶአል፤ እርሱ ንጹሕ ነው።
40 # 2ነገ. 2፥23። “የሰውም ጠጉር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። 41ጠጉሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። 42ዳሩ ግን በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ የለምጽ ደዌ ነው። 43ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሰውነቱ ቆዳ ላይ የሆነ የለምጽ ደዌ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ላይ ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቢሆን፥ 44በለምጽ ደዌ የተያዘ ሰው ነው፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ካህኑ፦ በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ላይ የሚገኝ ነው።
45 # ዘሌ. 10፥6። “የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው የሚለብሳቸው ልብሶች የተቀደዱ ይሁኑ፥ የራሱም ጠጉር የተጐሳቈለ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ እያለ ይጩኽ።#ሚክ. 3፥7። 46#ዘሌ. 14፥3፤ ዘኍ. 5፥2፤ 12፥14-15፤ 2ነገ. 7፥3-10፤ 15፥5፤ 2ዜ.መ. 26፥21፤ ማቴ. 26፥6፤ ማር. 14፥3፤ ሉቃ. 17፥11-19።በእርሱ ደዌው እስካለበት ጊዜያት ድረስ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር ውጪ ይሆናል።
47“የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢወጣ፥ ልብሱም የበግ ጠጉር ወይም በፍታ ቢሆን፥ 48በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጉር ቢሆን፥ በተለፋው ቆዳ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ቢሆን፥ 49ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በተለፋው ቆዳ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ ሆኖ ቢይታ፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ እዲያየው ይደረጋል። 50ካህኑም ደዌውን ያያል፤ ደዌውም ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ለይቶ ያስቀምጠዋል። 51በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በተለፋው ቆዳ ወይም ለማናቸውም አገልግሎት በሚውል የተለፋ ቆዳ ላይ ቢሰፋ፥ ደዌው እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነው፤ እርሱም ርኩስ ነው። 52ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጉር ወይም በፍታ ወይም ከተለፋው ቆዳ የሆነ ማናቸውም ደዌው ያለበት ነገር ላይ ቢሆን፥ እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነውና በእሳት ይቃጠል።
53“ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ባይሰፋ፥ 54ካህኑ ደዌ ያለበን ነገር እንዲያጥቡ ያዝዛል፤ ሌላም ሰባት ቀን ለይቶ ያስቀምጠዋል። 55ደዌው ያለበት ነገር ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ባይሰፋ ነገር ግን መልኩን ባይለውጥ፥ እርሱ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ የለምጽ ደዌው ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየሰፋ የሚሄድ ደዌ ነው።
56“ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ከታጠበ በኋላ ደዌው ቢከስም፥ ምልክቱ የነበረበትን ቦታ ከልብሱ ወይም ከተለፋው ቆዳ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው። 57በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ዳግም ቢታይ፥ እየሰፋ የሚሄድ ደዌ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር በእሳት ታቃጥለዋለህ። 58ነገር ግን አንተ ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ ከተሠራ ከማናቸውም ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል።
59 # ዘሌ. 14፥54-57። “ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለመወሰን እንዲቻል፥ በበግ ጠጉር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ የሚወጣ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ