የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 7

7
የአካን ኃጢአትነና ቅጣቱ
1 # ኢያ. 6፥18፤ 22፥20፤ 1ዜ.መ. 2፥7። የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ የጌታም ቁጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ።
2 # ዘኍ. 13፥17-20። ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ላከ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ፤” ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። 3ወደ ኢያሱም ተመልሰው እንዲህ አሉት፦ “ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፤ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም።” 4ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። 5የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን ገደሉ፤ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቁልቁለቱም ላይ ሳሉ መቱአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ።
6ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በጌታ ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 7ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ልትሰጠን ልታጠፋንም ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! 8ጌታ ሆይ! እስራኤል ከጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ እንግዲህ ምን እላለሁ? 9#ዘኍ. 14፥13-19።ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድነው?”
10ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ለምን በግምባርህ ተደፍተኽ ትሰግዳለህ? ቁም፤ 11#ኢያ. 6፥17-19።እስራኤል ኃጢአት ሠርቶአል፤ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። 12ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፤ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። 13#ኢያ. 3፥5፤ ዘሌ. 20፥7፤ 1ሳሙ. 16፥5።ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ ‘እስከ ነገ ተቀደሱ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና፦ “እስራኤል ሆይ! እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም።” 14ነገ ጧት በየነገዳችሁ ትቀርባላችሁ፤ ጌታም የሚለየው ነገድ በየወገኖቹ ይቀርባል፤ ጌታም የሚለየው ወገን በየቤተ ሰቦቹ ይቀርባል፤ ጌታም የሚለየው ቤተሰብ በየሰዉ ይቀርባል። 15#ዘዳ. 13፥15-16።እርም የሆነውም ነገር የተገኘበት ሰው የጌታን ቃል ኪዳን አፍርሶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ በደል ፈጽሟልና እርሱና የእርሱ የሆነው ነገር ሁሉ በእሳት ይቃጠል።’ ”
16ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እስራኤልንም በየነገዶቻቸው አቀረበ፤ የይሁዳም ነገድ ተለየ፤ 17#ዘኍ. 26፥20።የይሁዳንም ወገን አቀረበ የዛራንም ወገን ለየ፤ የዛራንም ወገን ሰዎች አንድ በአንድ አቀረበ፤ ዘንበሪም ተለየ፤ 18የቤቱንም ሰዎች አንድ በአንድ አቀረበ፤ ከይሁዳም ነገድ የሆነ የዛራ ልጅ የዘንበሪ ልጅ የከርሚ ልጅ አካን ተለየ። 19ኢያሱም አካንን እንዲህ አለው፦ “ልጄ ሆይ! ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝ።” 20አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “በእውነት በእስራኤል አምላክ በጌታ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ፤ 21በምርኮ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም ኀምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው።”
22ኢያሱም መልክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። 23ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፤ በጌታም ፊት አኖሩት። 24ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። 25#ኢያ. 6፥18፤ 22፥20፤ ዘዳ. 13፥15-16፤ 1ዜ.መ. 2፥7።ኢያሱም፦ “ለምን መከራን አመጣህብን? ጌታ ዛሬ መከራን ያመጣብሃል” አለው፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፤ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። 26#ኢያ. 8፥29፤ ዘዳ. 13፥18።በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ ጌታም ከጽኑ ቁጣው ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ