የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 3

3
እስራኤል ዮርዳኖስን መሻገሩ
1በማግስቱም ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፥ እርሱና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሰጢም ተነሥተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፤ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ። 2ከሦስት ቀንም በኋላ አለቆች በሰፈሩ መካከል አለፉ። 3#ዘኍ. 10፥33።ሕዝቡንም እንዲህ ብለው አዘዙ፦ “የአምላካችሁን የጌታን ቃል ኪዳን ታቦቱንና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ እርሱን በመከተል፥ 4በዚህ መንገድ በፊት አላለፋችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ ታውቃላችሁ። በእናንተና በታቦቱ መካከል ግን ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ።”
5ኢያሱም ሕዝቡን፦ “ነገ ጌታ በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ” አለ። 6ኢያሱም ካህናቱን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፉ፤” እነርሱም የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት ሄዱ።
7 # ኢያ. 1፥5፤ 4፥14፤ ዘዳ. 31፥23። ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን እንዲያውቁ በዚህ ቀን አንተን በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ከፍ ከፍ ማድረግ እጀምራለሁ። 8አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት እንዲህ ብለህ እዘዝ፦ ‘በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ።’ ”
9ኢያሱም ለእስራኤል ልጆች፦ “ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የጌታን ቃላት ስሙ” አለ። 10#ዘፀ. 33፥2፤ ዘዳ. 7፥1።ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደሆነ፥ እርሱም ከነዓናዊውን ኬጢያዊውንም ኤዊያዊውንም ፌርዛዊውንም ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ኢያቡሳዊውንም ከፊታችሁ ፈፅሞ እንደሚያሳድድ በዚህ ታውቃላችሁ። 11እነሆ፥ የምድር ሁሉ ጌታ ቃል ኪዳን ታቦት በፊታችሁ ወደ ዮርዳኖስ ያልፋል። 12#ኢያ. 4፥2፤ 4።እንግዲህ አሁን ከእስራኤል ነገዶች ዐሥራ ሁለት ሰዎች፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ምረጡ። 13እንዲህም ይሆናል፤ የምድርን ሁሉ ጌታ የጌታን ታቦት የተሸከሙ ካህናት የእግሮቻቸው ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም፥ ከላይ የሚወርደው የዮርዳኖስ ውኃ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል።”
14እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር። 15እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እጅግ ሞልቶ ነበርና ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ ሲደርሱ፥ ታቦቱንም የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ፥ 16#መዝ. 114፥3።ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ፤ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ። 17#ኢያ. 4፥7፤ 22።እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት በሚሻገሩ ጊዜ የጌታን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳንስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ