ትንቢተ ኢዩኤል 2
2
1የጌታ ቀን መጥቷልና፥ እርሱም ቀርቧልና በጽዮን መለከትን ንፉ፥ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ እሪ በሉ፥ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ። 2የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤ታላቅና ብርቱ ሕዝብ በተራሮች ላይ እንደ ወገግታ ተዘርግቶአል፥ ከዘለዓለምም ጀምሮ እንደ እነርሱ ያለ አልነበረም፥ ከእነርሱም በኋላ ለብዙ ትውልድ እንደ እነርሱ ያለ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። 3እሳት በፊታቸው ትባላለች፥ በኋላቸውም ነበልባል ታቃጥላለች፥ ምድሪቱ በፊታቸው እንደ ዔድን ገነት፥ በኋላቸውም የምድረ በዳ በረሃ ናት፥ ከእነርሱም የሚያመልጥ የለም።
4 #
ራእ. 9፥7-9። መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፥ እንደ ፈረሶችም ይሮጣሉ። 5በተራራ ላይ እንዳሉ ሰረገሎች ድምፅ፥ ገለባውንም እንደሚበላ እንደ እሳት ነበልባል ድምፅ፥ ለሰልፍም እንደ ተዘጋጀ እንደ ብርቱ ሕዝብ ያኰበኩባሉ። 6ከፊታቸው አሕዛብ ይንቀጠቀጣሉ፥ የሰውም ፊት ሁሉ ይጠቁራል። 7እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፥ እንደ ጦር ሰዎችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፥ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፥ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም። 8አንዱ ካንዱ ጋር አይጋፋም፥ እያንዳንዱም መንገዱን ይጠበጥባል፥ በጦር መሣርያ መካከል ያልፋሉ፥ የሚያስቆማቸው ነገር የለም። 9በከተማም ያኰበኩባሉ፥ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ፥ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፥ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ። 10#ራእ. 8፥12።ምድሪቱም ከፊታቸው ትናወጣለች፥ ሰማያትም ይንቀጠቀጣሉ፥ ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ። 11#ራእ. 6፥17።ጌታም በሠራዊቱ ፊት ድምፁን ያሰማል፥ ሠራዊቱ እጅግ ብዙ ነውና፥ ቃሉንም የሚፈጽም እርሱ ኃያል ነውና፥ የጌታ ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነውና ማንስ ይችለዋል?
12አሁንስ፥ ይላል ጌታ፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። 13ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፥ ጌታ አምላካችሁም ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ጽኑ ፍቅሩ የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። 14የሚመለስና የሚጸጸት እንደሆነ፥ ጌታ አምላካችሁም የእህልና የመጠጥ ቁርባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደሆነ ማን ያውቃል? 15በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ 16ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፥ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ። 17#1መቃ. 7፥36-38።የጌታም አገልጋዮች ካህናት ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ፦ “አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤” ከአሕዛብ መካከል፦ “አምላካቸው ወዴት ነው?” ስለምን ይበሉ?
18ጌታም ስለ ምድሩ ቀና፥ ለሕዝቡም ራራለት። 19ጌታም መልሶ ሕዝቡን፦ እነሆ፥ እህልንና ወይንን ዘይትንም እልክላችኋለሁ፤ እናንተም በእርሱ ትጠግባላችሁ፥ ከእንግዲህም ወዲያ በአሕዛብ መካከል መሰደቢያ አላደርጋችሁም። 20የሰሜንንም ሠራዊት ከእናንተ ዘንድ አርቃለሁ#2፥20 ከግብጽ በስተቀር ኃያላን የእስራኤል ጠላቶች ከሰሜን ነበር የሚመጡት።፥ ወደ በረሃና ወደ ምድረ በዳ፥ ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር#2፥20 የሙት ባሕር ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር#2፥20 ታላቁ ባሕር ወይም የሜዲተራንያ ባሕር አድርጌ አሳድደዋለሁ፥ እርሱም ብዙ ነገር አድርጎአልና ግማቱ ይወጣል፥ ክርፋቱም ይነሣል አለ።
21ምድር ሆይ፥ ጌታ ታላቅ ነገር አድርጎአልና አትፍሪ፥ ደስም ይበልሽ፥ እልልም በዪ። 22እናንተ የምድር እንስሶች ሆይ፥ የምድረ በዳው ማሰማርያ ለምልሞአልና፥ ዛፉም ፍሬውን አፍርቶአልና፥ በለሱና ወይኑም ኃይላቸውን ሰጥተዋልና አትፍሩ። 23እናንተ የጽዮን ልጆች፥ ጌታ አምላካችሁ ቀድሞ የሚደርሰውን ዝናብ ስለ ጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፥ እንደ በፊትም ቀዳሚውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦላችኋልና በእርሱ ደስ ይበላችሁ፥ ለእርሱም እልል በሉ። 24አውድማዎችም እህልን ይሞላሉ፥ መጥመቂያዎችም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፈስሳሉ። 25የሰደድሁባችሁ ታላቁ ሠራዊቴ አንበጣና ደጎብያ ኩብኩባና ተምች የበላቸውን ዓመታት እመልስላችኋለሁ። 26ብዙ መብል ትበላላችሁ፥ ትጠግቡማላችሁ፥ ከእናንተም ጋር ተአምራትን የሠራውን የጌታ የአምላካችሁን ስም ታመሰግናላችሁ፥ ሕዝቤም ለዘለዓለም አያፍርም። 27እኔም በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፥ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ፥ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፥ ሕዝቤም ለዘለዓለም አያፍርም።
28ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፥ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ወጣቶቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ 29ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎች ላይም መንፈሴን አፈስሳለሁ#2፥29 የእግዚአብሔር ስጦታ የሚቀርበት ማንም ሰው አይኖርም።፥ 30በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፥ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ ይሆናል። 31#ማቴ. 24፥29፤ ማር. 13፥24፤25፤ ሉቃ. 21፥25፤ ራእ. 6፥12፤13።ታላቁና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። 32#የሐዋ. 2፥17-21።#ሮሜ 10፥13።እንዲህም ይሆናል፥ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፥ ጌታም እንደ ተናገረ፥ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም የሚተርፉ ይኖራሉ። ደግሞም ጌታ የጠራቸው ይገኛሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢዩኤል 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ