መጽሐፈ ኢዮብ 39

39
1“የበረሃ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን?
ዋላይቱስ የምታምጥበትን ጊዜ ትመለከታለህን?
2ከእርሷ የሚወስዱባትንስ ወራት መቁጠር ትችላለህን?
የምትወልድበትንስ ጊዜ ታውቃለህን?
3ይንበረከካሉ፥ ልጆቻቸውንም ይወልዳሉ፥
ከምጣቸውም ያርፋሉ።
4ልጆቻቸው ይጠነክራሉ፥
በሜዳም ያድጋሉ፥
ይወጣሉ፥ ወደ እነርሱም አይመለሱም።
5የሜዳውንስ አህያ ማን ነፃ ለቀቀው?
የበረሃውንስ አህያ ከእስራቱ ማን ፈታው?
6በረሃውን ለእርሱ ቤት አድርጌ ሰጠሁት፥
መኖሪያውም በጨው ምድር ነው።
7በከተማ ውካታ ይስቃል፥
የነጂውን#39፥7 እንሰሳትን የሚነዳ ሰው። ጩኸት አይሰማም።
8ተራራውን እንደ መሰማርያው ይቃኘዋል፥
ለምለሙንም ሣር በሙሉ ይፈልጋል።
9ጐሽ ሊያገለግልህ ፈቃደኛ ነውን?
ወይስ በግርግምህ አጠገብ ያድራልን?
10ጐሽ እንዲተልምልህ ልታጠምደው ትችላለህን?
ወይስ ከአንተ በኋላ በእርሻ ላይ ይጐለጉላልን?
11ጉልበቱስ ብርቱ ስለ ሆነ በእርሱ ትታመናለህን?
አድካሚ ሥራህን ለእርሱ ትተዋለህን?
12ወደ አንተ እንደሚመለስና፥
ሰብልህንስ በአውድማህስ እንደሚያከማችልህ ትተማመናለህን?
13ምንም እንኳን እንደ ሸመላ ባትበርም፥
የሰጐን ክንፍ በደስታ ይንቀሳቀሳል፤
14እንቁላልዋን በመሬት ላይ ትተዋለች፥
በአፈርም ውስጥ ታሞቀዋለች፥
15እግር ሊሰብረው እንደሚችል፥
የምድረ በዳም አውሬ ሊረግጠው እንደሚችል ትረሳለች።
16የእርሷ ያልሆኑ ይመስል በልጆችዋ ትጨክናለች፥
ድካምዋ ከንቱም ሊሆን ቢችልም አትፈራም፥
17እግዚአብሔር ጥበብን ነሥቷታልና፥
ማስተዋልንም አላደላትምና።
18ወደ ላይ ከፍ ከፍ ስትል
በፈረስና በፈረሰኛው ትሳለቃለች።
19ለፈረስ ጉልበቱን ትሰጠዋለህን?
አንገቱንስ ጋማ ታለብሰዋለህን?
20እንደ አንበጣስ ታፈናጥረዋለህን?
ግርማዊ ማንኰራፋቱ እጅግ ያስፈራል።
21በሸለቆው ውስጥ በኮቴው ይጐደፍራል፥
በጉልበቱም ደስ ይለዋል፥
ሰይፍ የታጠቁትንም ለመጋፈጥ ይወጣል።
22በፍርሃት ላይ ይስቃል፥
በጭራሽ አይደነግጥም፥
ሰይፍም አያሸሸውም።
23በእርሱ ላይ የፍላጻ ኮረጆ፥ የሚብለጨልጭ ጦርና
ሰላጢን#39፥23 ትንሽ ጦር። ያንኳኳሉ።
24በነውጥና በቁጣ መሬትን ይውጣል፥
የመለከትም ድምፅ ቢሰማ አይቆምም።
25የመለከትም ድምፅ ሲሰማ፦ እሰይ! ይላል፥
ከሩቅ ሆኖ የሠራዊቱን ውካታ፥
ፍልምያውንና የአለቆቹን ጩኸት፥ ያሸታል።
26በውኑ ጭልፊት የሚያንዣብበው፥
ክንፎቹንስ ወደ ደቡብ የሚዘረጋው በአንተ ጥበብ ነውን?
27ንስር ከፍ ከፍ የሚለው፥
ቤቱንም በከፍታ ላይ የሚያደርገው በአንተ ተእዛዝ ነውን?
28የሌሊት መኖርያው ዓለት ነው፥
የዓለት ጫፍም መከላከያ ይሆነዋል።
29በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይቃኛል፥
ዐይኖቹም ከሩቅ ይመለከታሉ።
30 # ማቴ. 24፥28፤ ሉቃ. 17፥37። ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፥
በድን ባለበትም ስፍራ እርሱ በዚያ አለ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ