መጽሐፈ ኢዮብ 36

36
1ኤሊሁም ቀጠለ፤ እንዲህም አለ፦
2“ገና ስለ እግዚአብሔር የሚነገር አለኝና
ጥቂት ቆየኝ፥ እኔም አስታውቅሃለሁ።
3እውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥
ፈጣሪዬም ጻድቅ መሆኑን አሳይሃለሁ።
4ቃሌ በእውነት ሐሰት የለበትም፥
በእውቀትም ፍጹም የሆነ ከአንተ ጋር አለ።#36፥4 ኤሊሁ ስለ ራሱ እየተናገረ ነው።
5እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም፥
እርሱም በጥበባዊ ኃይሉም ጽኑ ነው።
6እርሱ በደለኛን በሕይወት አይጠብቅም፥
ለችግረኞች ግን ይፈርዳል።
7ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፥
ለዘለዓለምም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥
እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ።
8በሰንሰለት ቢታሰሩ፥
ወይም በችግር ገመድ ቢጠመዱ፥
9ተግባራቸውንና መተላለፋቸውን
በትዕቢትም እንደሚሠሩም ይናገራቸዋል።
10ጆሮአቸውን ለተግሣጽ ይከፍተዋል፥
ከክፋትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል።
11ከሰሙትና ካገለገሉት፥
ዕድሜአቸውን በብልጽግና፥
ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ።
12ባይሰሙ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ፥
ያለ እውቀትም ይሞታሉ።
13ልበ ደንዳኖች ግን ቁጣን ይወዳሉ፥
እርሱም ባሠራቸው ጊዜ አይጮኹም።
14በሕፃንነታቸው ሳሉ ይሞታሉ፥
ሕይወታቸውም በሰዶማውያን መካከል ይጠፋል።
15የተቸገረውን በችግሩ ያድነዋል፥
በመከራም እንዲሱሙ ያደርጋቸዋል#36፥15 ጆሮአቸውን ይከፍታል።
16እንዲሁም አንተን ከመከራ
ችግር ወደሌለበት ወደ ሰፊ ስፍራ በወሰደህ ነበር፥
በማዕድህም ላይ ቅባት የሞላበት ምግብ በተዘጋጀ ነበር።
17አንተ ግን የበደለኞች ፍርድ ደረሰብህ፥
ፍርድና ብይን እንደሚይዛቸው።
18ሀብት ወደ ስድብ አስቶ እንዳይወስድህ፥
ትልቅ ጉቦም ከመስመር እንዳያስወጣህ።
19ብልጽግናህና ኃይልህ በሙሉ
ከችግር የሚጠብቅህ ይመስልሃልን?
20ሰዎች ድንገት የሚሞቱበትን ሌሊትን አትመኛት።
21አሁን ከመከራ የምትፈተነው ለዚሁ ነውና፥
ወደ በደል እንዳትመለስ ተጠንቀቅ።
22እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ልዑል ነው፥
እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው?
23ማነው መንገዱን የሚያሳየው?
ወይስ፦ ‘ተሳስተሃል’ የሚለው ማን ነው?
24ይልቁንም ሰዎች የዘመሩለትን ሥራውን ማክበርን አስታውስ።
25ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፥
ሰውም ከሩቅ ያየዋል።
26እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም።
የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም።
27የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥
ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፥
28ደመናት ያዘንባሉ፥
በሰዎችም ላይ በገፍ ያፈሳሉ።
29የደመናውንም መዘርጋት፥
የማደሪያውንም ነጐድጓድ የሚያስተውል ማን ነው?
30እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል፥
የባሕሩንም ጥልቀት ይከድናል።
31በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፥
ብዙም ምግብ ይሰጣል።
32መብረቅን በእጆቹ ይይዛል፥
ያዘዘውንም እንዲመታ ያደርገዋል፥
33የነጐድጓድ ድምፅ ስለ እርሱ ይናገራል፥
እንስሶችም ደግሞ ስለሚመጣው ውሽንፍር ይጮኻሉ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ