የዮሐንስ ወንጌል 21:15-20, 22-25

የዮሐንስ ወንጌል 21:15-20 መቅካእኤ

ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ከእነዚህ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፤” አለው። ኢየሱስም “ግልገሎቼን አሰማራ፤” አለው። ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ፤” አለው። ለሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ለሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “በጎቼን አሰማራ። እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ቦታ ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል” አለው። በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብር ሲያመለክት ይህንን ተናገረ። ከዚያም “ተከተለኝ፤” አለው። ጴጥሮስም ዘወር ሲል ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ከበስተኋላው አየ፤ እርሱም በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ።

የዮሐንስ ወንጌል 21:22-25 መቅካእኤ

ኢየሱስም “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድስ፥ ምን ግድ አለህ? አንተ ተከተለኝ” አለው። ስለዚህ “ያ ደቀመዝሙር አይሞትም” የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰማ፤ ነገር ግን ኢየሱስ “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ ምን ግድ አለህ?” አለው እንጂ “አይሞትም፤” አላለውም ነበር። ስለ እነዚህም ነገሮች የመሰከረው፥ ይህንንም የጻፈው ይህ ደቀመዝሙር ነው፤ ምስክሩም እውነት እንደሆነ እናውቃለን። ኢየሱስም ያደረገው ሌላ ብዙ ነገር አለ፤ ሁሉም አንድ በአንድ ቢጻፍ፥ እንደሚመስለኝ፥ ዓለም እራሱ የሚጻፉትን መጻሕፍት ለመያዝ ቦታ አይበቃውም ነበር።