የዮሐንስ ወንጌል 19:19-42

የዮሐንስ ወንጌል 19:19-42 መቅካእኤ

ጲላጦስም ደግሞ ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ ጽሕፈቱም “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበረ። ኢየሱስም የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ነበረና ከአይሁድ ብዙዎች ይህን ጽሕፈት አነበቡት፤ በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ተጽፎ ነበር። ስለዚህ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን “እርሱ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ አለ ብለህ ጻፍ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ፤” አሉት። ጲላጦስም “የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” ብሎ መለሰ። ወታደሮቹም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ወታደር አንድ ክፍል እንዲደርስ በአራት ከፋፈሉአቸው፤ እጀ ጠባቡንም እንዲሁ ወሰዱ። እጀ ጠባቡ ግን ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። ስለዚህም እርስ በርሳቸው “ለማን እንዲሆን ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም “ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነበር። ወታደሮቹም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም እንዲሁም መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር። ኢየሱስም እናቱንና ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን “አንቺ ሴት ሆይ! እነሆ ልጅሽ” አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን “እናትህ እነኋት” አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከወዲሁ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉም ቃል ይፈጸም ዘንድ “ተጠማሁ” አለ። በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት። ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ እንዲሁም ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና፥ ሥጋቸው በሰንበት ቀን በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት። ወታደሮችም መጥተው ከተሰቀሉት ሰዎች መካከል የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤ ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ቀድሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤ ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ወጣ። ያየውም መስክሮአል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንደሚናገር ያውቃል። ይህ የሆነው “ከእርሱ አጥንት አይሰበርም” የሚለው የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። ደግሞም ሌላው የመጽሐፍ ክፍል “ያንን የወጉትን ያዩታል” ይላል። ከዚህም በኋላ፥ አይሁድን በመፍራት በስውር የኢየሱስ ደቀመዝሙር የነበረው የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። እንዲሁም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቶ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት። በተሰቀለበትም ስፍራ የአትክልት ቦታ ነበረ፤ በአትክልቱም ቦታ ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ። መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበረና የአይሁድ የዝግጅት ቀን ስለ ነበረ ኢየሱስን በዚያ አኖሩት።