ትንቢተ ኤርምያስ 33

33
ከቅጣት በኋላ ፈውስ
1ኤርምያስ ገና በእስር ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የጌታ ቃል ሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“ስሙ ጌታ የሆነ፥ ምድርንም የፈጠረ ጌታ፥#33፥2 ዕብራይስጡ እንዲህ ይላል፦ “የፈጠራት ጌታ፥ ሊያጸናትም የሠራት ጌታ።” ሊያጸናውም የሠራው ጌታ እንዲህ ይላል፦ 3ወደ እኔ ተጣራ፥ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቃቸውን ታላላቅና ስውር የሆኑ ነገሮችን እነግርሃለሁ። 4ከሰይፍ ፊትና ከከበባት የአፈር ድልድል ለመከላከል ስለ ፈረሱ ስለዚህች ከተማ ቤቶች፥ ስለ ይሁዳም ነገሥታት ቤቶች የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላልና፦ 5ከለዳውያን ጋር ለመዋጋት ወጥተዋል፤ ነገር ግን በቁጣዬና በመዓቴ በገደልኋቸው ሰዎች ሬሳዎች ሊሞሉአቸው ነው፥ ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፊቴን ከዚህች ከተማ ሰውሬአለሁና። 6እነሆ፥ ፈውስንና መድኃኒትን አመጣላታለሁ፥ እፈውሳቸዋለሁም፤ እጅግም የበዛ ሰላምንና እውነትን እገልጥላቸዋለሁ። 7የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ቀድሞም እንደ ነበሩ አድርጌ እሠራቸዋለሁ። 8በእኔም ላይ ከሠሩት ከበደላቸው ኃጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ፤ በእኔም ላይ ያመፁትንና የሠሩትን የበደላቸውን ኃጢአት ሁሉ ይቅር እላለሁ። 9የምሠራላቸውንም በጎነት ሁሉ በሚሰሙ የምድር አሕዛብ ሁሉ ፊት ይህች ከተማ ለእኔ የምስጋናና የክብር የደስታም ስም ትሆናለች፤ እኔም ስላደረግሁላት በጎነትና ሰላም ሁሉ ይፈራሉ ይንቀጠቀጣሉም።
10“ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናንተ፦ ‘ያለ ሰውና ያለ እንስሳ የሆነች ባድማ ናት’ በምትሉአት በዚህች ስፍራ፥ ሰውም በማይቀመጥባቸው፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባድማ በሆኑ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ ዳግመኛ ይህ ይሰማል 11#1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 5፥13፤ 7፥3፤ ዕዝ. 3፥11፤ መዝ. 100፥5፤ 106፥1፤ 107፥1፤ 118፥1፤ 136፥1።እርሱም፦ የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የሙሽራው ድምፅና የሙሽራይቱ ድምፅ፥ ወደ ጌታም ቤት፦ ‘ጌታ ቸር ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና የሠራዊት ጌታን አመስግኑ!’ እያሉ የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡ ሰዎች ድምፅ ነው። የምድሪቱን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥ ይላል ጌታ።
12“የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ባድማ ሆና፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ በሆነችው በዚህች ስፍራ፥ በከተሞችዋም ሁሉ መንጎቻቸውን የሚያሳርፉ የእረኞች መኖሪያ ስፍራ ዳግመኛ ይኖራል። 13በደጋው ላይ ባሉ ከተሞች፥ በቈላውም ባሉ ከተሞች፥ በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ በብንያምም አገር፥ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በጎቹ መንጋውን በሚቆጥረው ሰው እጅ ሥር እንደገና ያልፋሉ፥ ይላል ጌታ።
የጽድቅ ቁጥቋጥና ከዳዊት ጋር የተደረገ ቃል ኪዳን
14 # ኤር. 23፥5፤6። “እነሆ፥ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ። 15በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቁጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። 16በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም በደኅንነት ትቀመጣለች፤ እርሷም፦ ‘ጌታ ጽድቃችን ነው’ በሚለው ስም ትጠራለች። 17#2ሳሙ. 7፥12-16፤ 1ነገ. 2፥4፤ 1ዜ.መ. 17፥11-14።ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ዳዊት በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አያጣም፤ 18#ዘኍ. 3፥5-10።እንዲሁም ሌዋውያን ካህናት በእኔ ፊት የሚቃጠለውን መሥዋዕት የሚያቀርብ፥ የእህሉንም ቁርባን የሚያቃጥል፥ ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ፈጽሞ አያጡም።”
19የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 20“ጌታ እንዲህ ይላል፦ ቀንና ሌሊት በተመደበላቸው ጊዜ እንዳይሆኑ የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ 21በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከአገልጋዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። 22የሰማይን ሠራዊት መቁጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባርያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ።”
23የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24“ይህ ሕዝብ፦ ‘ጌታ የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል’ ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ ባለመሆኑ ሕዝቤን አቃልለዋል። 25ጌታ እንዲህ ይላል፦ የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያላጸናሁ እንደሆነ፥ 26በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች እንዲሆኑ ከዘሩ ላለመውሰድ፥ የያዕቆብንና የባርያዬን የዳዊትን ዘር እኔ ደግሞ እጥላለሁ። እኔ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸዋለሁምና።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ