ትንቢተ ኤርምያስ 22
22
ነቢዩ ኤርምያስ ንስሐ እንዲገቡ መምከሩ
1ጌታ እንዲህ አለ፦ “ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤት ውረድ በዚያም ይህን ቃል ተናገር፥ 2እንዲህም በል፦ በዳዊት ዙፋን የምትቀመጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! አንተና ባርያዎችህ፥ በእነዚህም በሮች የሚገባው ሕዝብህ፥ የጌታን ቃል ስሙ። 3ጌታ እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ። 4ይህንንም ነገር በጥንቃቄ ብታደርጉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታት፥ በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ ተቀምጠው፥ በዚህ ቤት በሮች ይገባሉ፤ እርሱም ባርያዎቹም ሕዝቡም እንዲሁ ይገባሉ። 5#ማቴ. 23፥28፤ ሉቃ. 13፥35።ነገር ግን እነዚህን ቃላት ባትሰሙ፥ ይህ ቤት ባድማ እንዲሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል ጌታ። 6ጌታ ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤት እንዲህ ይላልና፦ አንተ በእኔ ዘንድ እንደ ገለዓድና እንደ ሊባኖስ ራስ ነህ፥ ነገር ግን በእርግጥ ምድረ በዳ ማንም የማይቀመጥባቸውም ከተሞች አደርግሃለሁ። 7የጦር መሣሪያም የሚይዙትን አጥፊዎች በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ፥ የተመረጡትንም የዝግባ ዛፎችህን ይቈርጣሉ፥ በእሳትም ውስጥ ይጥሉአቸዋል። 8ብዙ አሕዛብም በዚህች ከተማ አጠገብ ያልፋሉ፥ ሁሉም ባልንጀሮቻቸውን፦ ጌታ በዚህች ታላቅ ከተማ ለምን እንዲህ አደርገ?” ይላሉ። 9እነርሱም፦ “የአምላካቸውን የጌታን ቃል ኪዳን ትተው ለሌሎች አማልክት ስለ ሰገዱ ስላገለገሉአቸውም ነዋ ብለው ይመልሳሉ።”
10የተወለደባትንም አገር ለማየት ከእንግዲህ ወዲህ አይመለስምና ለሚሄደው እጅግ አልቅሱ እንጂ ለሞተው አታልቅሱ አትዘኑለትም።
ወደ ኢዮስያስ ልጆች መልእክት መምጣቱ
11 #
2ነገ. 23፥31-34፤ 2ዜ.መ. 36፥1-4። በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ ስለ ነገሠው ከዚህም ስፍራ ስለ ወጣው ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎም ጌታ እንዲህ ይላልና፦ “ዳግመኛ ወደዚህ አይመለስም፥ 12በተማረከባት አገር በዚያ ይሞታል እንጂ፤ ይህችንም አገር ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።”
13“ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዓመፅ ለሚሠራ፥ ባልንጀራውንም እንዲያው በከንቱ ለሚያሠራ፥ ዋጋውንም ለማይሰጠው፤ 14‘ለራሴ ሰፊ ቤት ትልቅም ሰገነት እሠራለሁ’ ለሚል፥ መስኮቶችንም ለሚያወጣለት፥ በዝግባም ሥራ ለሚያስጌጠው፥ በቀይ ቀለምም ለሚቀባው ወዮለት! 15በዝግባ እንጨት ስለምትወዳደር በውኑ ትነግሣለህን? በውኑ አባትህ ይበላና ይጠጣ ፍርድንና ጽድቅን ያደርግ አልነበረምን? በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር። 16የድሀውንና የችግረተኛውን ፍርድ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖ ነበር። ይህ እኔን ማወቅ አይደለምን? ይላል ጌታ። 17ዓይንህና ልብህ ግን ለተጭበረበረ ትርፍ ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ ዓመፅንና ግፍንም ለመሥራት ብቻ ነው።” 18#2ነገ. 23፥36—24፥6፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7።ስለዚህ ጌታ ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፦ “ ‘ወንድሜ ሆይ! ወዮ! እህቴ ሆይ! ወዮ!’ እያሉ አያለቅሱለትም፥ ወይም፦ ‘ጌታ ሆይ! ወዮ! ግርማዊነቱ ሆይ! ወዮ!’ እያሉ አያለቅሱለትም። 19አህያም እንደሚቀበር ይቀበራል፥ ከኢየሩሳሌምም በር ወደ ውጭ ተጐትቶ ይጣላል።”
20“ውሽሞችሽ ሁሉ ጠፍተዋልና ወደ ሊባኖስ ወጥተሽ ጩኺ፤ በባሳን ላይ ድምፅሽን ከፍ አድርጊ፤ ከዓባሪምም#22፥20 ዓባሪም በደቡብ ምሥራቅ ዮርዳኖስ በሞዓብ ግዛት የሚገኝ ተራራማ ሥፍራ ነው። ሆነሽ ጩኺ። 21በደኅንነትሽ ጊዜ ተናገርሁሽ፤ አንቺም፦ ‘አልሰማም’ አልሽ። ከሕፃንነትሽ ጀምሮ ድምፄን አለመስማትሽ መንገድሽ ነው። 22እረኞችሽን ሁሉ ንፋስ ያሰማራቸዋል፥ ውሽሞችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ ኃጢአትሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ ትዋረጃለሽም። 23አንቺ በሊባኖስ የምትቀመጪ፥ በዝግባ ዛፍም ውስጥ ጎጆሽን የምትሠሪ ሆይ! ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሕመም በያዘሽ ጊዜ እንዴት ታቃስቻለሽ!”
በኢኮንያን ላይ የተደረገ ፍርድ
24 #
2ነገ. 24፥8-15፤ 2ዜ.መ. 36፥9፤10። “እኔ ሕያው ነኝና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ የማኅተም ቀለበት ቢሆን ኖሮ እንኳ፥ ከዚያ አውልቄ እጥልህ ነበር፥ ይላል ጌታ፤ 25ነፍስህንም ለሚሹት ለምትፈራቸውም እጅ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ለከለዳውያንም እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ። 26አንተንም የወለደችህንም እናትህን ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ አገር እጥላችኋለሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ። 27ለመመለስም ነፍሳቸው ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አይመለሱም።” 28በውኑ ይህ ሰው ኢኮንያን የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ ነውን? ወይስ እርሱ ማንም የማይፈልገው የሸክላ ዕቃ ነውን? እርሱና ዘሩስ በማያውቋት ምድር ስለምን ተወርውረው ተጣሉ? 29ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! ምድር ሆይ! የጌታን ቃል ስሚ። 30ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ ሰው ዘር የሚከናወንለት የለም፥ በዳዊትም ዙፋን ላይ የሚቀመጥ በይሁዳም የሚነግሥ ከእንግዲህ ወዲህ አይገኝምና፦ መካን በዘመኑም የማይከናወንለት ሰው ብላችሁ ጻፉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 22: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ