የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 21

21
ኢየሩሳሌም በናቡከደነፆር እጅ ሥር መውደቋ
1ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ ይህም የሆነው ንጉሡ ሴዴቅያስ የመልክያን ልጅ ጳስኮርንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል በላከበት ጊዜ ነው፦ 2#2ነገ. 25፥1-11፤ 2ዜ.መ. 36፥17-21።“የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋናልና ስለ እኛ፥ እባክህ፥ ጌታን ጠይቅ፤ ምናልባትም ጌታ ለእኛ እንደ ተአምራቱ ሁሉ አድርጐ ከእኛ እንዲመለስ ያደርገዋልና።”
3ኤርምያስም እንዲህ አላቸው፦ “ሴዴቅያስን እንዲህ በሉት፦ 4‘የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥ በቅጥርም ውጭ የከበቡአችሁን ከለዳውያንን የምትወጉበትን በእጃችሁ ያለውን የጦር መሣርያ እመልሳለሁ፥ እነርሱንም ወደዚህች ከተማ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ። 5እኔም በተዘረጋች እጅና በብርቱ ክንድ፥ በቁጣና በመዓት በታላቅም መቅሠፍት እወጋችኋለሁ። 6በዚህችም ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ሰዎችንና እንስሶችን እመታለሁ፥ በጽኑም ቸነፈር ይሞታሉ። 7ከዚህ በኋላ፥ ይላል ጌታ፥ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን፥ ከቸነፈርና ከሰይፍ ከራብም በዚህችም ከተማ የቀሩትን፥ አገልጋዮቹንና ሕዝቡን በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፥ አይራራላቸውም፥ አይምራቸውም።’
8“ለዚህም ሕዝብ እንዲህ በል፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በፊታችሁ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ አኑሬአለሁ። 9በዚህች ከተማ ውስጥ የሚቀር በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል፥ እርሱም በምርኮ ነፍሱን ያድናል። 10ለመልካም ሳይሆን ለክፉ ፊቴን በዚህች ከተማ ላይ አድርጌአለሁና፤ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች፥ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል፥ ይላል ጌታ።’
ለዳዊት ቤት መልእክት
11“የይሁዳ ንጉሥ ቤት ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ። 12የዳዊት ቤት ሆይ! ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ ሥራችሁ ክፋት ቁጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣና ማንም ሳያጠፋው እንዳይነድድ፥ በማለዳ ፍርድን አድርጉ፥ የተበዘበዘውንም ከጨቋኙ እጅ አድኑ።’ 13እነሆ፥ በሸለቆው ውስጥ በሜዳ ላይም ባለው አምባ የምትቀመጪ ሆይ! እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ፤ እናንተም፦ ‘በእኛ ላይ የሚወርድ ወይም ወደ መኖሪያችን የሚገባ ማን ነው?’ የምትሉ ሆይ! እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፤ 14እንደ ሥራችሁም ፍሬ እቀጣችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በጫካዋም ውስጥ እሳትን አነድዳለሁ፥ በዙሪያዋም ያለውን ሁሉ ይበላል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ