ትንቢተ ኤርምያስ 20
20
ጳስኮር ነቢዩ ኤርምያስን ማሳደዱ
1በጌታም ቤት የተሾመው አለቃ፥ የኢሜር ልጅ ካህኑ ጳስኮር ኤርምያስ በዚህ ነገር ትንቢት ሲናገር ሰማ። 2ጳስኮርም ነቢዩን ኤርምያስን መታው፥ በጌታም ቤት በነበረው በላይኛው በብንያም በር ባለው በመንቈር#20፥2 ከግንድ ተቦርቡሮ የሚሠራ የወንጀለኛ ማሠርያ። ውስጥ አሠረው። 3በነጋውም ጳስኮር ኤርምያስን ከመንቈር ውስጥ ፈታው። ኤርምያስም እንዲህ አለው፦ “ጌታ ስምህን፦ ማጎርሚሳቢብ#20፥3 ትርጓሜው “ሽብር በየስፍራው” ማለት ነው። እንጂ ጳስኮር ብሎ አይጠራህም። 4ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ ለራስህና ለወዳጆችህ ሁሉ ፍርሃት አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ ዐይኖችህም ያያሉ፤ ይሁዳንም ሁሉ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል በሰይፍም ይገድላቸዋል። 5የዚህችንም ከተማ ባለጠግነት ሁሉ ጥሪትዋንም ሁሉ ክብርዋንም ሁሉ የይሁዳንም ነገሥታት መዝገብ ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እነርሱም ይበዘብዙአቸዋል ይዘውም ወደ ባቢሎን ያመጡአቸዋል። 6አንተም፥ ጳስኮር ሆይ! በቤትህም የሚኖሩት ሁሉ ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ፤ አንተም በሐሰት ትንቢት የተናገርህላቸው ወዳጆችህ ሁሉ ወደ ባቢሎን ትገባላችሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ፥ በዚያም ትቀበራላችሁ።”
ነቢዩ ኤርምያስ ማጉረምረሙ
7አቤቱ! አታለልኸኝ እኔም ተታለልሁ፥ ከእኔም በረታህ አሸነፍህም፤ ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኛለሁ፥ ሁሉም ያላግጡብኛል። 8በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤ “ግፍና ጥፋት” ብዬ እጮኻለሁ፤ የጌታ ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና መዘበቻ ሆኖብኛልና። 9እኔም፦ “የጌታን ስም አላነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም” ብል፥ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፥ መሸከምም አልቻልሁም። 10የብዙ ሰዎችን የክፋት ሹክሹክታ ሰምቻለሁ፥ ማስፈራራትም ከብቦኛል። መውደቄን የሚጠብቁ የሰላሜ ሰዎች ሁሉ፦ “ምናልባት ይታለል እንደሆነ፥ እናሸንፈውም እንደሆነ፥ እርሱንም እንበቀል እንደሆነ፥ ክሰሱት እኛም እንከስሰዋለን” ይላሉ። 11ጌታ ግን እንደ አስፈሪ ተዋጊ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ አያሸንፉም፤ አይከናወንላቸውምና በጽኑ እፍረት ያፍራሉ፥ ለዘለዓለምም በማይረሳ ውርደት ይዋረዳሉ። 12የሠራዊት ጌታ ሆይ! ጻድቅን የምትመረምር ኩላሊትንና ልብን የምትመለከት፥ ሙግቴን ገልጬልሃለሁና በቀልህን በላያቸው ልይ። 13ለጌታ ዘምሩ ጌታንም አመስግኑ፤ የችግርተኛውን ነፍስ ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና።
14 #
ኢዮብ 3፥1-19። የተወለድሁባት ቀን የተረገመች ትሁን! እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን የተባረከች አትሁን! 15“ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል” ብሎ ለአባቴ የምሥራች ነግሮ እጅግ ደስ ያሰኘው ሰው የተረገመ ይሁን። 16ያም ሰው ጌታ ሳይጸጸት እንደ ገለበጣቸው ከተሞች ይሁን፥ በማለዳም ልቅሶን በቀትርም ጩኸትን ይስማ፤ 17እናቴ መቃብር እንድትሆነኝ ማኅፀንዋም ዘወትር ይዞኝ እንዲቆይ በማኅፀን ውስጥ አልገደለኝምና። 18ድካምንና ጣርን እንዳይ፥ ዘመኔም በእፍረት እንድታልቅ ለምን ከማኅፀን ወጣሁ?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 20: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ