የጌታ መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፥ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፥ ምድያማውያን እንዳያዩት ተደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። የጌታ መልአክ ተገልጦለት “አንተ ኃያል ጦረኛ! እነሆ፥ ጌታ ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ ጌታ ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘ጌታ ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን ጌታ ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ ጌታ ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፥ “ባለህ ኃይል ሂድ፤ እስራኤውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው” ጌዴዎንም፥ “ጌታ ሆይ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። ጌታም፥ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በእርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ ተመልሼ እስክመጣ፥ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” ጌታም፥ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው። ጌዴዎን ወደ ቤቱ ሄደ፤ የፍየል ጠቦትም ዐረደ፤ አንድ ኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ጋገረ። ሥጋውን በቅርጫት፥ መረቁን በምንቸት ይዞ በመምጣት በባሉጥ ሥር ለተቀመጠው አቀረበለት። የጌታ መልአክ፥ “ሥጋውን እርሾ ያልገባበትን ቂጣ ወስደህ፥ በዚያ ዐለት ላይ አኑር፤ መረቁንም በሥጋውና በቂጣው ላይ አፍስስ” አለው፤ ጌዴዎንም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ ተሰወረ። ጌዴዎን ያየው የጌታ መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የጌታን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ። ጌታም፥ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። ጌዴዎንም በዚያ ለጌታ መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “ጌታ ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል። በዚያች ሌሊት ጌታ ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል። በዚህ ፍርስራሽ ጉብታ ላይ ለአምላክህ ለጌታ የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።” ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር። ሌሊቱ ነግቶ የከተማው ሕዝብ ከመኝታው ሲነሣ፥ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ በአጠገቡ የቆመው የአሼራ ምስል ተሰባብሮ፥ አዲስ በተሠራው መሠዊያ ላይ ሁለተኛው ወይፈን ተሠውቶ ነበር። እነርሱም፥ “ይህን ያደረገ ማን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ነገሩን በጥብቅ ሲከታተሉም፥ “የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን መሆኑን ደረሱበት።” የከተማይቱም ሰዎች ኢዮአስን፥ “የበኣልን መሠዊያ ያፈረሰና በአጠገቡ የቆመውን የአሼራን ምስል ዐምድ የሰበረው ልጅህ በመሆኑ መሞት ስላለበት አውጣልን አሉት።” በዚህ ጊዜ ኢዮአስ በቊጣ ለገነፈለውና በዙሪያው ለነበረው ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ለበኣል ትሟገቱለታላችሁን? ልታድኑትስ ትሞክራላችሁን? ለእርሱ የሚሟገትለት ቢኖር እስከ ጠዋት ይሙት! እንግዲህ በኣል በእርግጥ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ሲያፈርሱበት ራሱን ሊከላከል ይችላል።” ስለዚህም፥ “መሠዊያውን አፍርሶበታልና ራሱ በኣል ይሟገተው” ሲሉ በዚያ ዕለት ጌዴዎንን፥ “ይሩበኣል” ብለው ጠሩት። በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ሁሉ፥ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች ያላቸውን አስተባብረው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር በኢይዝራኤል ሸለቆ ሰፈሩ። ከዚያም የጌታ መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ፤ እርሱም መለከት ነፋ፤ አቢዔዝራውያን እንዲከተሉት ጠራቸው። እንዲሁም በመላው የምናሴ ምድር መልእክተኞቹን ልኮ እንዲከተሉት ጥሪ አደረገ፤ ደግሞም የአሴር፥ የዛብሎንና የንፍታሌም ሰዎች ወጥተው እንዲገጥሟቸው መልእክተኛ ላከባቸው። ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “በተናገርኸው መሠረት እስራኤላውያንን በእጄ የምታድናቸው ከሆነ፥ እነሆ፤ የበግ ጠጉር ባዘቶ በአውድማው ላይ አኖራለሁ። ምድሩ በሙሉ ደረቅ ሆኖ ባዝቶው ላይ ብቻ ጤዛ ቢኖር፥ እንዳልከው እስራኤላውያንን በእኔ እጅ እንደምታድናቸው አውቃለሁ።” እንደዚሁም ሆነ፤ ጌዴዎን በማግስቱ ጠዋት ማልዶ ተነሣ፤ ባዘቶውንም ሲጨምቅ የወጣው ውሃ አንድ ቆሬ ሞላ። ከዚያም ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “እባክህ አትቈጣኝ፤ አንዲት ጥያቄ እንደገና ልጠይቅ። በጠጉሩ ባዘቶ ላይ ሌላ ሙከራ እንዳደርግ ፍቀድልኝ፤ በዚህ ጊዜ ምድሩ ሁሉ በጤዛ ተሸፍኖ ባዘቶው ደረቅ ይሁን።” በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር እንደጠየቀው አደረገ፤ ባዘቶው ብቻ ደረቅ ሲሆን፥ ምድሩ በሙሉ በጤዛ ተሸፍኖ ነበር።
መጽሐፈ መሳፍንት 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 6:11-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos