የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 6:11-40

መጽሐፈ መሳፍንት 6:11-40 አማ05

ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ “ዖፍራ” ተብላ ወደምትጠራው መንደር መጥቶ ከአቢዔዜር ጐሣ የተወለደው የኢዮአስ ንብረት በሆነው የወርካ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ምድያማውያን እንዳያዩት ተሸሽጎ በወይን መጭመቂያው ስፍራ የስንዴ ነዶ ይወቃ ነበር። በዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኀያልና ብርቱ ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ታዲያ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ ችግር እንዴት ሊደርስብን ቻለ? አባቶቻችን እንደ ነገሩን እግዚአብሔር ያደርገው የነበረ ድንቅ ሥራ ሁሉ ዛሬ የት አለ? ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸውም ነግረውን ነበር፤ ዛሬ ግን እግዚአብሔር እኛን በመተው እንደ ፈለጉ ያደርጉን ዘንድ ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጥቶናል።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሂድ፤ በዚህ ባለህ ብርቱ ኀይል ሁሉ በመጠቀም እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ አውጣ፤ እነሆ እኔ ራሴ ልኬሃለሁ” ሲል አዘዘው። ጌዴዎንም “ታዲያ እኔ እንዴት አድርጌ እስራኤልን ላድን እችላለሁ? ወገኔም ከምናሴ ነገድ መካከል እጅግ ደካማ ነው፤ እኔም ከቤተሰቤ መካከል በጣም አነስተኛ ነኝ” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም “እኔ ስለምረዳህ ይህን ማድረግ ትችላለህ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው ያኽል አድርገህ ታደቃቸዋለህ” አለው። ጌዴዎንም “በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፥ አንተ በእርግጥ እግዚአብሔር መሆንህን የሚያስረዳ ምልክት ስጠኝ፤ ምግብ የሚሆን ቊርባን እስካመጣልህም ድረስ እባክህ ከዚህ ስፍራ አትሂድ” አለው። እግዚአብሔርም “አንተ እስክትመለስ ድረስ እቈያለሁ” አለው። ጌዴዎንም ወደ ቤት ገባና የፍየል ጠቦት ዐርዶ አዘጋጀ፤ ዐሥር ኪሎ የሚያኽልም ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት እንጀራ ጋገረ፤ ሥጋውን በመሶብ፥ መረቁን በምንቸት አድርጎ በወርካው ሥር ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር መልአክ ወስዶ አቀረበለት። መልአኩም “ሥጋውንና እንጀራውን በዚህ አለት ላይ አስቀምጠህ መረቁን በላዩ አፍስስበት” ሲል አዘዘው፤ ጌዴዎንም እንደታዘዘው አደረገ። የእግዚአብሔር መልአክ ቀረብ ብሎ በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና እንጀራውን ነካ፤ እሳትም ከአለቱ ላይ ተነሥቶ ሥጋውንና እንጀራውን በላ፤ ከዚያም በኋላ መልአኩ ተሰወረ። ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን በተገነዘበ ጊዜ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! የአንተን መልአክ ፊት ለፊት አይቼአለሁ ወዮልኝ!” አለ። እግዚአብሔር ግን “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አይዞህ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። ጌዴዎንም በዚያ መሠዊያ ሠርቶ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው” ብሎ ሰየመው፤ (ይህም መሠዊያ እስከ ዛሬ የአቢዔዜር ጐሣ ይዞታ በሆነችው በዖፍራ ቆሞ ይገኛል።) በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “የአባትህን ኰርማና ሰባት ዓመት የሞላው አንድ ሌላ ኰርማ ውሰድ፤ አባትህ ለባዓል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ ያለውን ‘አሼራ’ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል ሰባብረህ ጣል፤ በዚያም የፍርስራሽ ጒብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በደንብ የተስተካከለ መሠዊያ ሥራ፤ ከዚያን በኋላ ሁለተኛውን ኰርማ ውሰድ፤ ሰባብረህ የጣልከውንም የአሼራን ምስል ስብርባሪ በማንደድ ኰርማውን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ።” ጌዴዎንም ከአገልጋዮቹ ዐሥሩን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተሰቡንና የከተማይቱን ኗሪዎች ከመፍራቱም የተነሣ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን በሌሊት ጨለማ ለብሶ ነበር። በማግስቱ የከተማይቱ ኗሪዎች ማልደው በተነሡ ጊዜ ለባዓል የተሠራው መሠዊያ መፍረሱንና የአሼራም ምስል ተሰባብሮ መውደቁን አዩ፤ ከዚያም በተሠራው መሠዊያ ላይ ሁለተኛው ኰርማ ታርዶ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡን ተመለከቱ። እርስ በርሳቸውም “ይህን ያደረገ ማን ነው?” በማለት ተጠያየቁ፤ ብዙ ከተመራመሩም በኋላ ይህን ያደረገው የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን መሆኑን ደረሱበት፤ ከዚህም በኋላ ኢዮአስን “የባዓልን መሠዊያ ስላፈረሰና በአጠገቡ ያለውንም የአሼራን ምስል ሰባብሮ ስለ ጣለ፥ እንዲሞት ልጅህን ወዲህ አውጣልን!” አሉት። ኢዮአስ ግን በቊጣ ተነሣሥተው በእርሱ ላይ የመጡትን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ለበዓል ትሟገታላችሁን? እርሱንስ ታድኑታላችሁን? ለእርሱ የሚሟገትለት ሁሉ እስከ ነገ ጧት ይገደላል፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ሰው ጋር ለራሱ እስቲ ይሟገት!” ከዚህ በኋላ ኢዮአስ “ፈራርሶ የወደቀው የእርሱ መሠዊያ ስለ ሆነ እስቲ ይችል እንደ ሆነ ባዓል ራሱን ይከላከል፤” ለማለት ፈልጎ፥ ለጌዴዎን ይሩባዓል የሚል ስም አወጣለት። ከዚያም በኋላ ምድያማውያን፥ ዐማሌቃውያንና የምሥራቅ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ፤ በኢይዝራኤል ሸለቆም ሰፈሩ። የእግዚአብሔር መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ፤ የአቢዔዜር ጐሣ ሰዎች ሁሉ እንዲከተሉት እነርሱን ለመጥራት እምቢልታ ነፋ፤ የምናሴን ነገድ ሁሉ መልእክት ልኮ ይከተሉት ዘንድ አስጠራቸው፤ እንዲሁም ወደ አሴር፥ ወደ ዛብሎንና ወደ ንፍታሌም ነገዶች መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ከሌሎቹ ጋር ለመሰለፍ ወጡ። ከዚህ በኋላ ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “እንደ ተናገርከው እስራኤልን በእኔ እጅ ታድን ዘንድ መርጠኸኛል። እነሆ! ስንዴ በምንወቃበት አውድማ ላይ የተባዘተ የበግ ጠጒር አስቀምጣለሁ፤ ነገ ጧት ሌላው ምድር ሁሉ ደረቅ ሆኖ በዚህ ጠጒር ባዘቶ ላይ ብቻ ጤዛ ከሆነ፥ እንደ ተናገርከው እስራኤልን ለማዳን የመረጥከኝ መሆኑን አረጋግጣለሁ።” ልክ እርሱ እንዳለውም ሆነለት፤ ጌዴዎን ጧት በማለዳ በተነሣ ጊዜ የበግ ጠጒሩን ባዘቶ ሲጨምቀው በአንድ መቅጃ የሚሞላ ውሃ ከውስጡ ወጣ። ቀጥሎም ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “እባክህ አትቈጣኝ፤ እንደገና አንድ ጊዜ እንድናገር ፍቀድልኝ፤ ይኸውም በበግ ጠጒሩ ባዘቶ ላይ ሌላ ምልክት እንዲታይ ልጠይቅ፤ በዚህን ጊዜ የጠጒሩ ባዘቶ ደረቅ ሆኖ በዙሪያው ያለው ምድር እርጥብ እንዲሆን አድርግልኝ።” በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ያንኑ ምልክት አደረገ፤ በማግስቱ ጧት የጠጒሩ ባዘቶ ደረቅ ሆኖ በዙሪያው ያለው መሬት ግን በጤዛ ርሶ ተገኘ።