ትንቢተ ኢሳይያስ 62
62
1ጽድቅዋ እንደ ጸዳል መዳንዋም እንደሚበራ ፋና እስኪ ወጣ ድረስ፥ ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም አላርፍም። 2አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የጌታም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። 3በጌታ እጅ የውበት አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ። 4ከእንግዲህ ወዲህ፦ የተተወች አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፦ ውድማ አትባልም፤ ነገር ግን ጌታ ደስታዬ ባንቺ ነው ብሏታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፦ ደስታዬ የሚኖርባት ትባያለሽ ምድርሽም፦ ባል ያገባች ትባላለች። 5ጎልማሳም ድንግሊቱን እንደሚያገባ፥ እንዲሁ ልጆችሽ ያገቡሻል፤ ሙሽራም በሙሽራይቱ ደስ እንደሚለው፥ እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል። 6ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም። እናንት ወደ ጌታ አቤት፤ አቤት የምትሉ፤ ፈጽሞ አትረፉ፤ 7ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ለእርሱም ዕረፍት አትስጡት። 8ጌታ፦ ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፤ 9ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል ጌታንም ያመሰግናሉ፥ ያከማቹትም በመቅደሴ አደባባይ ላይ ይጠጡታል ብሎ በቀኙና በኃይሉ ክንድ ምሏል። 10እለፉ፥ በበሮች በኩል እለፉ፤ የሕዝቡንም መንገድ ጥረጉ፤ አዘጋጁ፥ ጎዳናውን አዘጋጁ፥ ድንጋዮቹንም አስወግዱ፤ ለአሕዛብም ዓርማ አሳዩ። 11#ኢሳ. 40፥10፤ ራእ. 22፥12።እነሆ፥ ጌታ ለምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል፦ ለጽዮን ልጅ፦ “እነሆ፥ መድኃኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር፥ ሥራውም በፊቱ አለ” በሏት። 12“ጌታ የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፥ “የተፈለገች፥ ያልተተወችም ከተማ” ትባያለሽ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 62: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ