ትንቢተ ኢሳይያስ 57:1-21

ትንቢተ ኢሳይያስ 57:1-21 መቅካእኤ

ጻድቅ ይሞታል፥ ማንም ልብ አይለውም፤ ምሕረተኞችም ይወገዳሉ፥ ጻድቃን ከክፉ እንዲድኑ መወሰዳቸውን ማንም አያስተውልም። ወደ ሰላም ይገባል፤ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል። እናንተ የአስማተኛይቱ ልጆች፥ የአምንዝራውና የጋለሞታይቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ። በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ? እናንተ በባሉጥ ዛፎች መካከል በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች በፍትወት የምትቃጠሉ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ሕፃናትን የምታርዱ፥ የዓመፅ ልጆችና የሐሰት ዘር አይደላችሁምን? በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣዎችሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቁርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቁርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣም? ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፥ መሥዋዕትንም ትሠዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ። ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፥ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፤ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፥ ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ። ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፥ ሽቱሽንም አበዛሽ፥ መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፥ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ። በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፥ ነገር ግን፦ ተስፋ የለም አላልሽም፤ የጉልበትን መታደስ አገኘሽ፥ ስለዚህም አልዛልሽም። ሐሰትን የተናገርሺው እኔንም ያላሰብሽው፥ በልብሽም ነገሩን ያላኖርሺው፥ ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔ ብዙ ጊዜ ዝም አልሁ፥ አንቺም አልፈራሽም። እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፥ ሥራሽም አይረዳሽም። ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፤ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። በእኔ የታመነ ግን ምድሪቱን ይገዛል፥ የተቀደሰውንም ተራራዬን ይወርሳል። እርሱም፦ “ጥረጉ፥ መንገድን አዘጋጁ፥ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አስወግዱ” ይላል። ለዘለዓለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፦ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘለዓለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም። ኃጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቁጣ ከእርሱ ሰወርኩ፤ እርሱ ግን በመንገዱ ገፋበት። መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እሰጣለሁ። የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፤ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል ጌታ። ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ሊል አይችልምና፥ ውኆቹም ጭቃና ጉድፍ ያወጣሉ። ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ።