ትንቢተ ኢሳይያስ 55

55
1 # ራእ. 21፥6፤ 22፥17። እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። 2#ሲራ. 24፥19-22።እንጀራ ላልሆነ ነገር ገንዘብን ለምን ታባክናላችሁ፥ የድካማችሁንም ዋጋ በማያጠግብ ነገር ለምን ትለውጣላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። 3#የሐዋ. 13፥34።ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ሰውነታችሁ በሕይወት እንድትኖር ስሙኝ፥ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘለዓለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። 4እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ። 5እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ ጌታ የማያውቅህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣል።
6ጌታ በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ 7ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ ጌታም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፤ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። 8አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል ጌታ። 9ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። 10#2ቆሮ. 9፥10።ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ እንድታበቅልና እንድታፈራም እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ፥ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ 11ከአፌ የሚወጣ ቃል እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል፤ የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። 12እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልል ይላሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። 13በእሾህም ፈንታ ጥድ፥ በኩርንችትም ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ ለጌታም መታሰቢያና ለዘለዓለምም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ