ትንቢተ ኢሳይያስ 1

1
1 # 2ነገ. 15፥1-7፤ 2ዜ.መ. 26፥1-23፤ 2ነገ. 15፥32-38፤ 2ዜ.መ. 27፥1-9፤ 2ነገ. 16፥1-20፤ 2ዜ.መ. 28፥1-27፤ 2ነገ. 18፥1—20፥21፤ 2ዜ.መ. 29፥1—32፥33። በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፤ በኢዮአታም፤ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን፤ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ።
የይሁዳ ሕዝብ አለመታዘዝ
2ሰማያት ሆይ፤ ስሙ! ምድር ሆይ፤ አድምጪ! ጌታ እንዲህ ተናግሮአልና፤
“ልጆች ወለድሁ፤ አሳደግኋቸውም፤ እነርሱ ግን ዐመጹብኝ።
3በሬ ጌታውን፤ አህያ የባለቤቱን ጋጥ ያውቃል፤
እስራኤል ግን አላወቀም፤ ሕዝቤም አላስተዋለም።”
4እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፤ በደል የሞላበት ወገን፤
የክፉ አድራጊ ዘር፤ ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ!
ጌታን ትተዋል፤ የእስራኤልን ቅዱስ አቃለዋል፤
ጀርባቸውንም በእርሱ ላይ አዙረዋል።
5ለምን ዳግመኛ ትመታላችሁ? ለምንስ በዐመፅ ትጸናላችሁ? ራሳችሁ በሙሉ ታሞአል፤ ልባችሁ ሁሉ ታውኮአል። 6ከእግር ጥፍራችሁ እስከ ራስ ጠጉራችሁ ጤና የላችሁም፤ ቁስልና ዕባጭ እንዲሁም እዥ ብቻ ነው፤ አልታጠበም፤ አልታሰረም፤ በዘይትም አልለዘበም።
7አገራችሁ ባድማ፤ ከተሞቻችሁ በእሳት የተቃጠሉ ይሆናሉ፤
ዐይናችሁ እያየ መሬታችሁ በባዕድ ይነጠቃል፤ ጠፍም ይሆናል።
8የጽዮን ሴት ልጅ በወይን አትክልት ውስጥ እንዳለ ዳስ፤
በዱባ ተክል ወስጥ እንደሚገኝ ጐጆ፤ እንደ ተከበበም ከተማ ተተወች።
9 # ዘፍ. 19፥24፤ ሮሜ 9፥29። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፤
እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር።
10እናንተ የሰዶም ገዦች፤ የጌታን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሰዎች፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አድምጡ። 11#አሞጽ 5፥21-22።“የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው?” ይላል ጌታ። የሚቃጠለውን የአውራ በግና የሰቡ እንስሳትን ስብ ጠግቤአለሁ፤ በበሬ፤ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም ደስ አልሰኝም። 12በፊቴ ለመቅረብ ስትመጡ፤ ይህን ሁሉ እንድታመጡ፤ የመቅደሴን ደጅ እንድትረግጡ ማን ጠየቃችሁ? 13ከንቱውን መባ አታቅርቡ፤ ዕጣናችሁን እጸየፋለሁ፤ የወር መባቻ በዓላችሁን፤ ሰንበቶቻችሁን፤ ጉባኤያችሁንና በክፋት የተሞላውን ስብሰባችሁን መታገሥ አልቻልሁም። 14የወር መባቻችሁንና የተደነገጉ በዓሎቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፤ መታገሥም አልቻልሁም። 15እጆቻቸሁን ለጸሎት ወደ እኔ ስትዘረጉ፤ ዐይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ፤ አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል፤ 16ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤ ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አርቁ፤ ክፉ ማድረጋችሁን ተዉ፤ 17መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፤ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ። 18“ኑና፤ እንዋቀስ” ይላል ጌታ፤ “ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል። 19እሺ ብትሉ፤ ብትታዘዙም የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ 20እምቢ ብላችሁ ብታምፁ ግን ሰይፍ ይበላችኋል።” የጌታ አፍ ይህን ተናግሮአልና። 21ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት አመንዝራ እንደ ሆነች ተመልከቱ! ቀድሞ ፍትሕ የሞላባት፤ ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤ አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ማደሪያ ሆነች! 22ብርሽ ዝጎአል፤ ምርጥ የወይን ጠጅሽ ውሃ ገባው፤ 23ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጉቦን ይወዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም። 24ስለዚህ ጌታ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ኀያል እንዲህ ይላል፤ “በባላንጣዎቼ ላይ ቁጣዬን እገልጣለሁ፤ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ። 25እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ ዝገትሽን ፈጽሜ አጠራለሁ፤ ጉድፍሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ። 26ፈራጆችሽን እንደ ጥንቱ፤ አማካሪዎችሽንም እንደ ቀድሞው እመልሳለሁ፤ ከዚያም የጽድቅ መዲና፤ የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ። 27ጽዮን በፍትሕ፤ በንስሓ የሚመለሱ ነዋሪዎቿም በጽድቅ ይዋጃሉ። 28ዐመፀኞችና ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይደቅቃሉ፤ ጌታንም የሚተዉ ይጠፋሉ። 29ደስ በተሰኛችሁባቸው የባሉጥ ዛፎች ታፍራላችሁ፤ በመረጣችኋቸውም የአትክልት ቦታዎች ትዋረዳላችሁ። 30ቅጠሉ እንደ ጠወለገ ወርካ፤ ውሃም እንደሌለው የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁ። 31ብርቱ ሰው እንደ ገለባ፤ ሥራውም እንደ ብልጭታ ይሆናል፤ ሁለቱም አብረው ይቃጠላሉ፤ እሳቱንም የሚያጠፋው የለም።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ