ትንቢተ ሆሴዕ 8
8
የእስራኤል ክህደት
1መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፤ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና እንደ ንስር በጌታ ቤት ላይ እያንዣበበ ነው። 2እነርሱም፦ “አምላክ ሆይ! እኛ እስራኤል እናውቅሃለን!” ብለው ወደ እኔ ጮሁ። 3እስራኤል በጎነትን ጥሎአል፤ ጠላትም ያሳድደዋል። 4ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም ሾሙ፥ እኔም አላወቅሁም፤ ለመጥፊያቸው ከብራቸውና ከወርቃቸው ጣዖታትን ለራሳቸው ሠሩ። 5ሰማርያ ሆይ! እምቦሳህን አስወግጃለሁ፤ ቁጣዬ በላያቸው ነድዶአል፤ መንጻት የማይቻላቸው እስከ መቼ ድረስ ነው? 6የተሠራው ነገር ከእስራኤል ዘንድ ነው፤ እርሱም በሞያተኛ የተሠራ ነው፤ እርሱም አምላክ አይደለም፤ የሰማርያም እምቦሳ ይሰባበራል። 7ነፋስን ዘሩ፥ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፤ የቆመውም እህል ዛላ የለውም፥ ከእርሱም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም እንኳ ባዕዳን ይበሉታል።
8እስራኤል ተውጦአል፤ አሁን በአሕዛብ መካከል እንደ ረከሰ ዕቃ ሆነዋል። 9ብቻውን እንደሚንከራተት የምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም ወዳጆችን በገንዘብ ቀጥሯል። 10ከአሕዛብ መካከል ወዳጆችን በገንዘብ ቢቀጥሩም እንኳ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ በቶሎ ይመነምናሉ።
11ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያዎችን አብዝቶአልና የኃጢአት መሥርያ መሠዊያዎች ሆነውለታል። 12በሺዎች የሚቆጠሩትን ሕጎቼን ጽፌለት እንኳ እንደ እንግዳ ነገር ተቆጠሩ። 13የተመረጠውን መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ ጌታ ግን በእነርሱ ደስ አይሰኝም፤ በደላቸውን አሁን ያስታውሳል፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸዋል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። 14እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ ቤተ መንግሥቶችን ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በእርሱ ከተሞች ላይ እሳት እልካለሁ፥ የንጉሥ ቅጥሮቹንም ትበላለች።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 8: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ