ትንቢተ ሆሴዕ 7
7
1በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በገላጣም ስፍራ ወንበዴ ቀምቶአልና፤ እስራኤልን በፈወስሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። 2እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንደማስታውስ ልብ አላደረጉም፤ አሁንም ሥራዎቻቸው ከብበዋቸዋል፥ እነርሱም በፊቴ አሉ። 3ንጉሡን በክፋታቸው፥ ሹማምንቱንም በሐሰታቸው ደስ ያሰኛሉ። 4ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ የተለወሰውን ቡኮ እስኪቦካ ድረስ ጋጋሪ እሳቱን ሳይቆሰቁሰው እንደ ተወው እንደ ጋለ ምድጃ ናቸው። 5በንጉሣችን ቀን ሹማምንቱ ከወይን ጠጅ ሞቅታ የተነሣ ታመሙ፤ እርሱም ከፌዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ። 6በሴራቸው ልባቸው እንደ ምድጃ ተቃጥላለችና፤ ጋጋሪያቸው ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በነጋም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ነደደ። 7ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም አጥፍተዋል፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወድቀዋል፤ ከእነርሱም መካከል ወደ እኔ የጮኸ የለም።
8ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ሆነ። 9ባዕዳን ጉልበቱን በዘበዙ፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም። 10የእስራኤልም ትዕቢት በራሱ ላይ መስክሮአል፤ ወደ አምላካቸው ወደ ጌታ ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም።
በአሕዛብ ላይ መደገፍ ከንቱ መሆኑ
11ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌለው እንደ ሞኝ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ። 12በመሄድ ላይ ሳሉ መረቤን በላያቸው እዘረጋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ በጉባኤያቸው ላይ እንደተላለፈው እገሥጻቸዋለሁ። 13ከእኔ ሸሽተው ሄደዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐምፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ እታደጋቸው ነበር፥ እነርሱ ግን ሐሰትን ተናገሩብኝ። 14በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዓመፁ። 15ክንዳቸውን ያስተማርሁና ያጸናሁ እኔ ነበርሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን አሴሩብኝ። 16ከንቱ ወደ ሆነው ነገር ተመለሱ፤ እንደ ረገበ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከክፉ አንደበታቸው የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ