ትንቢተ ሆሴዕ 10
10
የእስራኤል ኃጢአት እና ምርኮ
1እስራኤል ፍሬውን የሚሰጥ የተትረፈረፈ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያዎችን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ብልጥግና መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል። 2ልባቸው ሐሰተኛ ነው፤ በደላቸውን አሁን ይሸከማሉ፤ ጌታ መሠዊያዎቻቸውን ይሰባብራል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል። 3አሁንም፦ “ጌታን አልፈራንምና ንጉሥ የለንም፤ ንጉሥስ ለእኛ ምን ያደርግልናል?” ይላሉ።
4የማይረባውን ቃላት ተናገሩ፤ በሐሰት መሐላ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ስለዚህ መርዛም አረም በእርሻ ትልሞች ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት በቀለባቸው። 5የሰማርያ ሰዎች የቤትአዌንን እምቦሳ ፈሩ፤ ክብሩ ከእርሱ ተለይቶታልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም እሪ ብለው ይጮኹለታል። 6እርሱም ደግሞ ለታላቁ ንጉሥ እጅ መንሻ እንዲሆን ወደ አሦር ተማርኮ ይወሰዳል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። 7ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንደሚሳፈፍ ስንጥር ትጠፋለች። 8#ሉቃ. 23፥30፤ ራእ. 6፥16።የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾኽና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ እነርሱም ተራሮችን፦ “ሸፍኑን!” ኮረብቶችንም፦ “ውደቁብን!” ይሉአቸዋል።
9 #
መሳ. 19፥1-30። እስራኤል ሆይ! ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በዓመፀኛ ልጆች ላይ በጊብዓ ጦርነት አይደርስባቸውምን? 10በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ እጥፍ ስለ ሆነው በደላቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ በእነርሱ ላይ ይሰበሰቡባቸዋል። 11ኤፍሬም ማበራየት የምትወድ የተገራች ጊደር ነበር፥ እኔም በውብ አንገትዋ ላይ አልጫንኩባትም#10፥11 አንዳንድ ትርጉሞች ጫንኩባት ይላሉ።፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም ለራሱ አፈሩን ያለሰልሳል።
12 #
ኤር. 4፥3። ጌታ መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የመሻት ዘመን ነውና ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፥ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ሰብስቡ፥ ያልታረሰ መሬታችሁን እረሱ። 13ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና። 14በሕዝብህ መካከል ሽብር ይነሣል፤ ምሽጎችህም ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ሰልማን ቤትአርብኤልን በጦርነት ቀን እንዳፈረሰ፥ እናትም ከልጆችዋ ጋር ተዳምጣ ነበር። 15ቤቴል ሆይ! ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ እንዲሁ ይደረግባችኋል፤ ጎሕ ሲቀድ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ