የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ዕብራውያን 2

2
ታላቁ የማዳን ሥራ
1ስለዚህ ከሰማነው ነገር ተንሸራትተን እንዳንወድቅ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባል። 2በመላእክት የተነገረው ቃል በጽናት ከተረጋገጠ፥ እያንዳንዱም መተላለፍ ወይም አለመታዘዝ ትክክለኛውን ቅጣት ከተቀበለ፥ 3እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ ይህንኑ አረጋግጠውልናል። 4እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት።
5ስለ እርሱ የምንናገርለት፥ የሚመጣውን ዓለም ያስገዛው ለመላእክት አይደለምና። 6#መዝ. 8፥4-6።እንዲያውም በአንድ ስፍራ እንዲህ ተብሎ ተመስክሯል፦
“ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው?
ወይስ ትጠነቀቅለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው?
7ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤
የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንክለት፤
በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምከው፤
8ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፤”
ሁሉን ከእርሱ በታች ባስገዛ ጊዜ ያልተገዛለት ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና አላየንም፤ 9ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሁላችን ሞትን እንዲቀምስ፥ ከመላእክት ለጥቂት ጊዜ ዝቅ ብሎ የነበረውን፥ የሞትን መከራ በመቀበሉ ምክንያት የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖ ኢየሱስን እናየዋለን።
10ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ፥ ሁሉ ነገር በእርሱና ለእርሱ የተፈጠረው፥ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ተገብቷልና። 11የሚቀድሰውና በእርሱም የተቀደሱት ሁሉ መገኛቸው ከአንድ ነውና፤ ከዚህ የተነሣ ወንድሞች ብሎ ሲጠራቸው አያፍርም፤ 12#መዝ. 22፥23።እንዲህም በማለት፥
“ስምህን ለወንድሞቼ አበሥራለሁ፤
በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤”
13 # ኢሳ. 8፥17፤ ኢሳ. 8፥18። እንዲሁም፥
“እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤”
ደግሞም
“እነሆኝ እኔ፥ እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች” ይላል።
14እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፥ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ እርሱም ዲያብሎስ ነው። 15በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ታስረው የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ 16#ኢሳ. 41፥8፤9።የአብርሃምን ዘር ለመርዳት እንጂ ትኩረቱ ለመላእክት አይደለም። 17ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። 18ምክንያቱም እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ