ወደ ዕብራውያን 11:9-16

ወደ ዕብራውያን 11:9-16 መቅካእኤ

ለባዕድ አገር እያለም በተስፋ ቃል በተሰጠው ምድር፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ወራሾች እንደሆኑት እንደ ይስሐቅና እንደ ያዕቆብ በእምነት በድንኳን ኖረ፤ ምክንያቱም መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበር። ሣራም ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደሆነ ስለ ቈጠረች፥ ምንም እንኳን መካን ብትሆን፥ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፥ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ተቈጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከርቀት አይተውት ሰላምታ አቀረቡለት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩም እንግዶችና መጻተኞች ለመሆንም ታመኑ። እንደዚህ የሚሉት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ ያመለክታሉ። ያን ትተውት የወጡትን አገር አስበው ቢሆን ኖሮ፥ ወደዚያ የመመለስ እድል በነበራቸው ነበር። አሁን ግን የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና አምላካቸው ተብሎ ለመጠራት በእነርሱ አያፍርም።