ትንቢተ ሐጌ 2
2
የቤተ መቅደሱ የወደፊት ክብር
1በሰባተኛው ወር ከወሩም በሀያ አንደኛው ቀን የጌታ ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2ለይሁዳ ገዢ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ለታላቁ ካህን ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፥ ለቀሩትም ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ 3#ዕዝ. 3፥12።በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምንም አይደለምን? 4አሁን ግን፥ ዘሩባቤል ሆይ፥ በርታ፥ ይላል ጌታ፤ ታላቁ ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፥ በርታ፤ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፥ በርቱ፥ ይላል ጌታ፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ሥሩ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 5#ዘፀ. 29፥45፤46።ከግብጽ ምድር በወጣችሁ ጊዜ የገባሁላችሁ ቃል ነው መንፈሴ በመካከላችሁ ይቆማልና አትፍሩ። 6#ዕብ. 12፥26።የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እንደገና በቅርብ ጊዜ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ፤ 7መንግሥታትን ሁሉ አናውጣለሁ፥ በመንግሥታት ሁሉ ውድ የሆነ ዕቃም ይመጣል፤ ይህንንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 8ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 9የዚህ የኋለኛው ቤት ክብር ከፊተኛው ይልቅ ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
ተግሣጽና ቃል ኪዳን
10በዳርዮስ ዘመን በሁለተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በሀያ አራተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ሐጌ እንዲህ ሲል መጣ፦ 11የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ሕጉ ካህናቱን ጠይቅ፤ 12አንድ ሰው የተቀደሰ ሥጋ በልብሱ ዕጥፋት ቢይዝ፥ ዕጥፋቱ እንጀራ ወይም ወጥ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ዘይት፥ ወይም ማናቸውንም መብል ቢነካ ያ የተነካው የተቀደሰ ይሆናልን? ካህናቱም፦ አይሆንም ብለው መለሱ። 13#ዘኍ. 19፥11-22።ሐጌም፦ በሬሳ የረከሰ ሰው ከእነዚህ አንዱን ቢነካ ያ የተነካው በውኑ ይረክሳልን? አለ። ካህናቱም፦ አዎን ይረክሳል ብለው መለሱ። 14ሐጌም መልሶ እንዲህ አለ፦ ይህ ሕዝብና ይህ ወገን በፊቴ እንዲሁ ነው፥ ይላል ጌታ፤ የእጆቻቸውም ሥራ ሁሉ እንዲሁ ነው፤ በዚያ ያቀረቡትም ርኩስ ነው። 15አሁንም ከዛሬ ጀምራችሁ ወደ ፊት ልብ አድርጉ፥ በጌታ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመቀመጡ በፊት፥ 16በዚያን ጊዜ አንድ ሰው ሀያ መስፈሪያ ወዳለበት ምርት መጣ፥ የተገኘው ግን ዐሥር መስፈሪያ ብቻ ነው፤ አምሳ ማድጋ ለመቅዳት ወደ ወይን መጥመቂያው መጣ፥ የተገኘው ግን ሀያ ብቻ ነው። 17እጆቻችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፥ በአረማሞ፥ እና በበረዶ መታኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል ጌታ። 18ከዛሬው ከዘጠነኛው ወር ከሀያ አራተኛው ቀን ጀምራችሁ የሚመጣውን ጊዜ ልብ በሉ፤ የጌታ መቅደስ መሠረት ከተጣለበት ቀን ጀምሮ ልብ አድርጉ። 19ዘር በጎተራ አሁንም አለን? ወይንና የበለስ ዛፍ ሮማንና የወይራ ዛፍ አላፈሩም፤ ከዚህች ቀን ጀምሬ እባርካችኋለሁ።
እግዚአብሔር ለዘሩባቤል የሰጠው ተስፋ
20ከወሩ በሀያ አራተኛው ቀን የጌታ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሐጌ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21ለይሁዳ ገዢ ለዘሩባቤል እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ሰማያትንና ምድርን አናውጣለሁ፤ 22የመንግሥታትንም ዙፋን እገለብጣለሁ፥ የአሕዛብ መንግሥታትን ኃይል አጠፋለሁ፤ ሰረገሎችንና ነጂዎቻቸውን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችንና ፈረሰኞቻቸው እያንዳንዱ በወንድሙ ሰይፍ ይወድቃሉ። 23በዚያ ቀን ይላል የሠራዊት ጌታ፥ ባርያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፥ እወስድሃለሁ፥ ይላል ጌታ፥ እንደ ማተሚያ ቀለበት አደርግሃለሁ፥ እኔ መርጬሃለሁና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሐጌ 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ