የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሐጌ 1

1
ቤተ መቅደሱ ዳግም እንዲታነጽ የወጣ ትእዛዝ
1 # ዕዝ. 4፥24—5፥2፤ 6፥14። በንጉሡ በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ ወደ ይሁዳ ገዢ ወደ ሰላትያል ልጅ ወደ ዘሩባቤልና ወደ ታላቁ ካህን ወደ ኢዮሴዴቅ ልጅ ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕዝብ፦ ዘመኑ አልደረሰም፥ የጌታ ቤት የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም ይላል።” 3የጌታ ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ 4ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በታጠሩ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? 5አሁንም የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። 6ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልሰከራችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ለማስቀመጥ ደመወዙን ተቀበለ።
7የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። 8በእርሱ ደስ እንዲለኝና እንድከበርበት፥ ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትን አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ። ይላል ጌታ። 9እናንተ ብዙ ነገርን ፈልጋችሁ፥ እነሆ ጥቂት ሆነ፤ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። በምን ምክንያት? ይላል የሠራዊት ጌታ። ምክንያቱም እናንተ ሁሉ ወደ እየቤታችሁ እየሮጣችሁ የእኔ ቤት ስለፈረሰ ነው። 10ስለዚህ ሰማያት በላያችሁ ጠልን ከልክለዋል፥ ምድሪቱም የምታበቅለውን ከልክላለች። 11እኔም በምድሪቱና በተራሮች፥ በእህልና በአዲሱ ወይን፥ በዘይትና ምድር በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በከብቶች ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ።
12የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ታላቁ ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን የጌታን ድምፅ የነቢዩንም የሐጌን ቃል ሰሙ፥ አምላካቸው ጌታ ልኮታልና፤ ሕዝቡም በጌታ ፊት ፈሩ። 13የጌታ መልእክተኛ ሐጌ በጌታ መልእክት ሕዝቡን፦ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል ጌታ” ብሎ ተናገረ። 14ጌታም የይሁዳን ገዢ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፥ የታላቁን ካህን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስና የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አስነሣ፤ መጥተውም የአምላካቸውን የሠራዊትን ጌታ ቤት ሠሩ። 15ይህም በንጉሡ በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት፥ በስድስተኛው ወር ከወሩም በሀያ አራተኛው ቀን ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ