ትንቢተ ዕንባቆም 2
2
ለነቢዩ አቤቱታ መልስ
1በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ ምን እንደሚለኝና በአቤቱታዬም ምን መልስ እንደምሰጥ ለማየት እጠባበቃለሁ። 2ጌታም መለሰልኝ፥ እንዲህም አለ፦ ራእዩን ጻፍ፤ የሚያነበው እንዲሮጥ በጽላት ላይ በግልፅ አድርገው። 3#ዕብ. 10፥37።ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይፈጥናል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ጠብቀው፤ አይዘገይም።
4 #
ሮሜ 1፥17፤ ገላ. 3፥11፤ ዕብ. 10፥38። እነሆ፥ እርሱ ኮርቶአል፥ ነፍሱ በውስጡ ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። 5በእርግጥ ወይን አታላይ ነው፤ ትዕቢተኛ ሰው በስፍራው አርፎ አይቀመጥም፤ ስስቱን እንደ ሲኦል ያሰፋል፥ እርሱም እንደ ሞት አይጠግብም፤ አሕዛብንም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበስባል፥ ወገኖቹንም ሁሉ ወደ እርሱ ያከማቻል።
የክፉ ሰው ኀዘን
6እነዚህ ሁሉ፦ ለእርሱ ያልሆነውን ወደ እርሱ ለሚሰበስብ መያዣውንም ለራሱ የሚያበዛ ወዮለት! እስከ መቼ ነው? እያሉ ምሳሌ አይመስሉበትምን? 7አበዳሪዎችህ ድንገት አይነሡምን? የሚያንቀጠቅጡህ አይነቁምን? ለእነርሱም ብዝበዛ ትሆናለህ። 8አንተ ብዙ አሕዛብን በዝብዘሃልና፥ የሰውን ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርሷም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል።
9ከክፉ ለመታደግ ጐጆውን በከፍታ ላይ በማድረግ፥ ለቤቱ ክፉ ትርፍን የሚሰበስብ ወዮለት! 10ብዙ ሕዝቦችን ቆራርጠህ ለቤትህ እፍረትን መክረሃል፥ በነፍስህም ላይ ኃጢአትን አድርገሃል። 11ድንጋይ ከግንብ ውስጥ ይጮኻል፥ እንጨትም ከወራጅ ይመልስለታል።
12ከተማን በደም ለሚሠራ፥ ከተማንም በበደል ለሚመሠርት ወዮለት! 13#ሲራ. 14፥19።እነሆ፥ አሕዛብ ለእሳት እንደሚሠሩ፥ ሕዝቦችም ለከንቱነት እንደሚደክሙ ከሠራዊት ጌታ ዘንድ የሆነ አይደለምን? 14#ኢሳ. 11፥9።ውኃ ባሕርን እንደሚከድን፥ ምድር የጌታን ክብር በማወቅ ትሞላለችና።
15ኀፍረተ ሥጋውን ለማየት ባልንጀራውን ለሚያጠጣ፥ ክፉንም ለሚጨምርበት፥ ለሚያሰክረውም ወዮለት! 16በክብር ፈንታ እፍረት ሞልቶብሃል፤ አንተ ደግሞ ጠጣ፥ እንዳልተገረዘም ተቆጠር፤ የጌታ የቀኙ ጽዋ በአንተ ላይ ይመለስብሃል፥ እፍረትም በክብርህ ላይ ይሆናል። 17ከሰው ደም፥ በምድሪቱ፥ በከተማይቱና በእርሷም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ከተደረገው ዓመጽ የተነሣ፤ በሊባኖስ ላይ የተደረገው ዓመጽ ይከድንሃል፤ የአራዊትም ጥፋት ያስፈራቸዋል።
18ሠሪው የቀረጸውና ቀልጦ የተሠራ ምስል የውሸት አስተማሪ ነውና፤ ዲዳ ጣዖትን በመሥራት ሠሪው በሠራው ይታመናልና፤ የተቀረጸ ምስል ምን ይጠቅማል? 19እንጨቱን “ንቃ” ዝም ያለውንም ድንጋይ “ተነሣ” ለሚለው ወዮለት! ይህ ያስተምራልን? እነሆ፥ በወርቅና በብር ተለብጦአል፥ በውስጡም ምንም እስትንፋስ የለበትም። 20ጌታ ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድሪቷ ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል።
Currently Selected:
ትንቢተ ዕንባቆም 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ