ኦሪት ዘፍጥረት 44
44
የዮሴፍ ዋንጫ በብንያም ስልቻ ውስጥ መገኘት
1ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ ሲል መመሪያ ሰጠው፤ “የሰዎቹ ስልቻ የሚይዘውን ብር በየስልቻቸው አፍ ክተተው። 2ከዚያም የብር ዋንጫዬን በታናሹ ወንድማቸው ስልቻ አፍ ከእህሉ ዋጋ ጋር ጨምረው።” አዛዡም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። 3ጎሕ ሲቀድ ሰዎቹ ከነአህዮቻቸው ተሸኙ። 4ከከተማው ምንም ያህል ርቀው ሳይሄዱ፥ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፦ “እነዚያን ሰዎች ቶሎ ድረስባቸውና፥ ‘ለበጎ ነገር ስለምን ክፉ መለሳችሁ? 5ይህ ጌታዬ የሚጠጣበት፥ የተሰወረ ነገርም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? የፈጸማችሁት ድርጊት ክፉ ነው’” በላቸው። 6የቤቱ አዛዥም እንደ ደረሰባቸው፥ ልክ እንደተባለው ተናገራቸው። 7እነርሱ ግን እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን እንዲህ ያለ ነገር ለምን ይናገራል? እኛ አገልጋዮችህ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። 8ከዚህ ቀደምም በየስልቾቻችን አፍ የተገኘውን ብር ከከነዓን እንኳ መልሰን አምጥተናል፤ ታዲያ አሁን ብር ወይም ወርቅ ከጌታህ ቤት እንዴት እንሰርቃለን? 9የጠፋው ዕቃ ከአገልጋዮችህ የተገኘበት ይሙት፤ የቀረነው የጌታችን ባሮች እንሁን።” 10እርሱም “መልካም ነው፤ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባርያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ከበደሉ ነጻ ትሆናላችሁ” አላቸው። 11እያንዳንዱ ሰው ጭነቱን ወዲያውኑ አራግፎ ስልቻውን ፈታ። 12ከዚያም አዛዡ ፍተሻውን ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም፥ ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ። 13በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን በኀዘን ቀደዱ፤ ሁሉም ስልቾቻቸውን በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማዪቱ ተመለሱ።
14ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ፥ እርሱ ገና ከቤቱ አልወጣም ነበር። እነርሱም ከፊቱ መሬት ላይ ተደፉ። 15ዮሴፍም፥ “ለምን እንዲህ ያለ ነገር አደረጋችሁ? እንደ እኔ ያለ ሰው ስውር ነገርን የሚያውቅበት ልዩ ጥበብ እንዳለው አታውቁምን?” ሲል ጠየቃቸው። 16ይሁዳም፥ “ከእንግዲህ ለጌታችን ምን ማለት እንችላለን? ምንስ እንመልሳለን? እንዲህ ካለው በደል ንጹሕ መሆናችንን ማስረዳትስ እንዴት ይቻለናል? እግዚአብሔር የእኛን የአገልጋዮችህን በደል ገልጦአል፤ ከእንግዲህ ጽዋው የተገኘበት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሮችህ ነን” አለ። 17ዮሴፍም፥ “ይህንንስ ፈጽሞ አላደርገውም፤ ባርያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ብቻ ነው፤ የቀራችሁት በሰላም ወደ አባታችሁ ተመለሱ” አላቸው።
የይሁዳ ገላጋይነት
18ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፥ “ጌታዬ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፤ አንተም የፈርዖን ያህል የተከበርህ ስለሆንህ፥ እባክህን እኔን አገልጋይህን አትቈጣኝ። 19ጌታዬ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቈ ነበር። 20እኛም፥ ‘አዎን፥ ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፤ ወንድምየው ሞቷል፤ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወደዋል’ ብለንህ ነበር። 21ከዚያም አንተ አገልጋዮችህን፥ ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልኸን። 22እኛም ለጌታዬ ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም፤ ከተለየው ደግሞ አባትየው ይሞታል’ አልንህ። 23አንተ ግን እኛን አገልጋዮችህን፥ ‘ታናሽ ወንድማችሁ አብሮአችሁ ወደዚህ ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ አልኸን። 24እኛም ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ በተመለስን ጊዜ አንተ ጌታዬ ያልኸንን ነገርነው። 25ከዚያም አባታችን ‘እስቲ ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን’ ሲለን፤ 26‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን አብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በስተቀር፥ የሰውየውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው። 27አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤ 28አንዱ በወጣበት በመቅረቱ፥ “በእርግጥ የአውሬ እራት ሆኖአል” አልሁ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይኸው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቶአል። 29አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጉዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመሪር ኀዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’ 30እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ፥ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ስለ ሆነ፥ 31የልጁን ከእኛ ጋር አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ኀዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን። 32እኔ አገልጋይ፥ ‘ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር፥ ለዘለዓለም በደለኛ አድርገህ ቁጠረኝ’ በማለት፥ ስለ ልጁ ደኅንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ። 33ስለዚህ አሁን፥ አገልጋይህ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባርያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ። 34ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? ፈጽሞ አላደርገውም፤ እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 44: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ