የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 43

43
የያዕቆብ ልጆች ብንያምን ይዘው እንደገና ወደ ግብጽ መሄዳቸው
1ራቡ አሁንም በምድሪቱ ላይ እንደ ጸና ነበር፤ 2ከግብጽ ያመጡትንም እህል በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ አባታቸው “እስቲ እንደገና ወርዳችሁ፥ ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው። 3ይሁዳ ግን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎ በጥብቅ አስጠንቅቆናል፤ 4ወንድማችን ከእኛ ጋር እንዲወርድ ከፈቀድህ ወደዚያ ሄደን እህል እንሸምትልሃለን፤ 5እርሱን የማትልከው ከሆነ ግን እኛም ወደዚያ አንወርድም፤ ያም ሰው፥ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎናል።” 6እስራኤልም፥ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። 7እነርሱም፥ “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደገናም ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታድያ፥ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት። 8ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋር ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፥ አንተም፥ እኛም፥ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን። 9ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኀላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘለዓለም በደለኛ እኔ ልሁን። 10ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፥ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።” 11ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፤ ምድሪቱ ከምታፈራው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፥ ጥቂት ማር፥ ሽቱ፥ ከርቤ ተምርና ለውዝ በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው እጅ መንሻ ውሰዱለት። 12በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፥ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል። 13ወንድማችሁንም ይዛችሁ ወደ ሰውዬው በቶሎ ሂዱ። 14ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ይዛችሁ ለመመለስ እንድትችሉ ሁሉን የሚችል አምላክ በምሕረቱ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼንም ባጣ ምን አደርጋለሁ፤ ያመጣውን እቀበላለሁ።”
ከዮሴፍ ጋር መገናኘት
15የእስራኤልም ልጆች እጅ መንሻውን፥ የብሩን ዕጥፍ እንዲሁም ብንያምን ይዘው ተነሡ፤ ወደ ግብጽም በፍጥነት ወረዱ፤ ዮሴፍም ፊት ቀረቡ።
16ዮሴፍ ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ፥ “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ይዘሃቸው ሂድ፤ ዛሬ ቀትር ላይ አብረውኝ ስለሚበሉ ፍሪዳ ተጥሎ ምሳ ይዘጋጅ” አለው። 17አዛዡም ዮሴፍ የነገረውን አደረገ፤ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። 18የእስራኤልም ልጆች ወደ ዮሴፍ ቤት በመወሰዳቸው ፈሩ፤ እነርሱም፥ “ወደዚህ የመጣነው፥ ቀደም ሲል እዚህ መጥተን ስንመለስ በየስልቾቻችን ውስጥ ተመልሶ በተጨመረው ብር ሰበብ ነው። ሰውዬው ጥቃት ሊፈጽምብን፥ አስገድዶ ባሮቹ ሊያደርገንና አህዮቻችንን ሊቀማን ይፈልጋል” ብለው ሠጉ። 19ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥ ቀርበው፥ በቤቱ መግቢያ ላይ አነጋገሩት፤ 20እንዲህም አሉት፦ “ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤ 21ነገር ግን ለዐዳር በሰፈርንበት ቦታ የየስልቾቻችንን አፍ ስንከፍት፥ እያንዳንዳችን በስልቾቻችን አፍ ላይ፥ ብራችንን ሙሉውን አገኘነው። ገንዘቡንም ይኸው መልሰን ይዘን መጥተናል። 22አሁንም እህል መሸመቻ የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ ያኔ ገንዘቡን በየስልቾቻችን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት። 23የቤቱ አዛዥም፥ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ ነው፤ እኔ እንደሆንኩ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። 24ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው። የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው። 25ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነግሯቸው ስለ ነበር፥ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ።
26ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ ያመጧቸውን እጅ መንሻዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት። 27ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፤ ከዚያም “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው። 28እነርሱም መልሰው፥ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው” በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው በአክብሮት እጅ ነሡት። 29ዮሴፍ በዐይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየና፥ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፥ “ልጄ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለው። 30ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለ ተነካ፥ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰወር ያለ ቦታም ፈልጎ፥ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ። 31ፊቱን ከታጠበ በኋላ፥ ተመልሶ፥ ስሜቱን በመቈጣጠር፥ “ማእድ ይቅረብ” አለ። 32ለዮሴፍ ለብቻው ቀረበለት፤ ለወንድሞቹም ለብቻቸው ቀረበላቸው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ግብፃውያን ደግሞ ሌላ ገበታ ቀረበላቸው፤ ምክንያቱም ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብሮ መመገብን እንደ ጸያፍ ይቈጥሩት ነበር። 33ወንድማማቾቹ ከበኩሩ እስከ ታናሹ እንደየዕድሜአቸው በዮሴፍ ፊት በተርታ ተቀምጠው ነበር፤ በመገረምም እርስ በርሳቸው ተያዩ። 34ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ፥ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ አምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ አብረውት ተደሰቱ፤ እስኪረኩም ጠጡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ