ኦሪት ዘፍጥረት 40
40
ዮሴፍ የፈርዖን ሹማምንት ሕልም መፍታቱ
1ከዚህም በኋላ የግብጽ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊና እንጀራ ቤቱ ጌታቸውን የግብጽን ንጉሥ በደሉት። 2ፈርዖንም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ ቤቱ አዛዥ፥ በሁለቱም ሹማምንቱ ላይ ክፉኛ ተቈጣ፤ 3በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደ ተጋዘበትም እስር ቤት አስገባቸው። 4የዘበኞቹም አለቃ እስረኞቹን ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም በሚያስፈልጋቸው ይረዳቸው ነበር። እስር ቤት ገብተው ጥቂት እንደቈዩም፥ 5ታስረው የነበሩት የግብጽ የንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፥ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም አዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍቺ ነበረው። 6በማግስቱ ጧት ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲገባ ተክዘው አገኛቸው። 7ስለዚህም፥ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ኀዘን ይነበባል?” በማለት አብረውት በጌታው ግቢ የታሰሩትን የፈርዖን ሹማምንት ጠየቃቸው። 8እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጉምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት። ዮሴፍም፥ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር የሚገኝ አይደለምን? እስቲ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።
9ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ “ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤ 10ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈጥቊጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ። 11የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።” 12ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤ 13በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፥ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠዋለህ። 14እንግዲህ፥ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፥ እኔን አስበህ ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤ 15ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በአፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።”
16የእንጀራ ቤት አዛዡም፥ ለመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ሕልም፥ የተሰጠው ፍቺ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፥ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፤ ሦስት መሶቦች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ 17በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፤ ወፎችም ራሴ ላይ ካለው መሶብ ይበሉ ነበር።” 18ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ 19በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።” 20በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምንቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምንቱ ካሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው። 21የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር፤ 22የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው ሰቀለው። 23የሆነው ሆኖ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 40: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ