ኦሪት ዘፍጥረት 37:26-36

ኦሪት ዘፍጥረት 37:26-36 መቅካእኤ

ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድነው? ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና።” ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት። የምድያም ነጋዶችም አለፉ፥ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጉድጓድ አወጡት፥ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሃያ ብር ሸጡት፥ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት። ሮቤል ወደ ጉድጓዱ በተመለሰ ጊዜ፥ እነሆ ዮሴፍ በጉድጓድ የለም፥ ልብሱንም ቀደደ። ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፦ “ብላቴናው የለም፤ እኔስ ወዴት ልሂደው?” አለ። የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። ብዙ ኅብር ያለበትንም ልብሱን ወደ አባታቸው ወስደው “እነሆ፥ ይህን አገኘን የልጅህ ልብስ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እይ” አሉት። እርሱም ለይቶ ስላወቀው፦ “የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል” አለ። ያዕቆብ ልብሱንም ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፥ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ፦ “ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ።” አባቱም እንደዚህ ስለ እርሱ አለቀሰ። እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብጽ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጶጥፋራ ሸጡት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}