ወደ ገላትያ ሰዎች 1:11-20

ወደ ገላትያ ሰዎች 1:11-20 መቅካእኤ

ወንድሞች ሆይ! በእኔ የተሰበከላችሁ ወንጌል ከሰው እንዳልሆነ አስታውቃችኋለሁ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ እንጂ ከሰው አልተቀበልሁትም ወይም አልተማርሁትም። የአይሁድ እምነት ተከታይ በነበርኩበት ጊዜ እንዴት እንደ ኖርኩ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ከመጠን በላይ አሳድድና አጠፋ እንደ ነበር ሰምታችኋል፤ ለአባቶች ወግ ከመጠን በላይ ቅናት ስለ ነበረኝ፥ በአይሁዳዊነት ወገኖቼ ከነበሩት እኩዮቼ ብዙዎችን እበልጥ ነበር። ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል ወንጌሉን እንድሰብክ፥ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፤ ወይም ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወደ አረብ አገር ሄድሁ፤ እንደገና ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከዚያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፥ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ተቀመጥሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በስተቀር ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም። ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።